ምክር ቤቱ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን እና የኢጋድ ማቋቋሚያ ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ

12 Days Ago
ምክር ቤቱ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን  እና የኢጋድ ማቋቋሚያ ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን አፀደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን እና የበይነ መንግሥታዊ የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል።
 
በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን እንዲሁም የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል።
 
ረቂቅ አዋጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት ከሚቀይረው ፖሊሲ የመነጨ መሆኑ ተገልጿል።
 
የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ(ዶ/ር)፤ የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት በአምራች ዘርፉ ተወስኖ የነበረውን አሠራር በማስፋት ስብጥር ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
 
ሰብሳቢዋ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተሰጡ የማሻሻ ሀሳቦችን አካተው ለምከር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን፤ በምክር ቤቱ አባላት አስተያየቶች ከታከሉበት በኋላ አዋጅ 1322/2016 ሆኖ እንዲጸድቅ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል፡፡
 
የልዩ ኢኮኖሚ ዞን መቋቋሙ የአምራች ዘርፉን አቅም ለማሳደግ እድል የሚፈጥር እና የተቀናጀ የልማት አካሄድን ለማሳለጥ እንደሚጠቅምም ተጠቅሷል፡፡
 
በተጨማሪም መሰረተ ልማቶችን በተሻለ መልኩ ለማሟላት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ የአካባቢ ተፅዕኖን ለመቀነስ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ዶክተር አማረች ገልጸዋል፡፡
 
አዋጁ በርካታ ተቋማት እና ባለሀብቶች በዘርፉ ልማት በአምራች ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ እና ከዚህ ቀደም ለአልሚዎች ክፍት ያልነበሩ ሥራዎች ክፍት የሚሆኑበትን እድል እንደሚፈጥርም ተነግሯል።
 
ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ጠንካራ አደረጃጀት ተፈጥሮለት የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በተሻለ መልኩ ለመስጠትም ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
 
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የበይነ መንግሥታዊ የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ማቋቋሚ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን አዋጅ 1323/2016 አድርጎ አጽድቋል፡፡
 
የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረ በመሆኑ አብራርቷል።
 
በመሆኑም አሁን ካለው ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አኳያ መሻሻል አስፈላጊ ስለመሆኑ ያነሱ ሲሆን ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ መክሮ የተሻሻለውን ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top