ራስ አባተ ቧ ያለው (አባ ይትረፍ)

155 Days Ago
ራስ አባተ ቧ ያለው (አባ ይትረፍ)

በዓድዋ ጦርነት በጣም ጎልተው ከታዩት አብሪ ኮከቦች መካከል ጀግናው ራስ አባተ ቧ ያለው እንዱ ናቸው። በ1865 ዓ.ም በመንዝና ግሼ የተወለዱት ራስ አባተ በፈረስ ስማቸው ‘አባ ይትረፍ’ ይባላሉ። የጦር ገበሬው አባ ይትረፍ በሙያቸው የተመሰገኑ እና መድፍን እንደ በትር በእጃቸው መዳፍ እንዳሻቸው የሚያገላብጡ ጀግና ነበሩ። አባ ይትረፍ ዓድዋ የዘመቱት በ23 ዓመታቸው መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ።

የዓድዋ ጦርነትና ድል ሲነሣ ምንጊዜም አብሮ የሚነሣ እና የኢትዮጵያውያን የጀግንነትና የብልሃት ማሳያ የሆነው የመቐለው ምሽግ ውጊያ ነበር። ጣሊያኖች የመረብ ወንዝን ተሻግረው ወደ ትግራይ ሲገቡ ጠንካራ ምሽግ ከሠሩባቸው ቦታዎች አንዱ መቐለ እንዳ ኢየሱስ ነበር። ምሽጉን ማጆር ቶዞሊ አስጀምሮት እርሱ በአላጌው ውጊያ ሲሞት ማጆር ጋልያኖ አጠናቅቆታል። ለመቐለው ምሽግ መጠናከር ዋናው ምክንያት ጣሊያኖች አላጌ ላይ በራስ መኮንን በሚመራው የኢትዮጵያ ጦር የገጠማቸው ሽንፈት ነው። ጄኔራል አርሞንዲ ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም የደረሰበትን የአላጌን ግንባር ሽንፈት ተከትሎ ወደ ኋላ በሸሸው የጣሊያን ሠራዊት አማካኝነት ከባሕር ወለል በላይ በ2 ሺህ 240 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የእንዳ ኢየሱስ ምሽግ የበለጠ እንዲጠናከር አደረገ። በቦታው የሚገኘውን የኢየሱስን ታቦት አስወጥቶ ቦታውን ሙሉ በሙሉ ምሽግ አደረገው።

ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው፥ "የመቐለ ምሽግ በደቡብ በኩል 3 ሜትር ስፋት ያለው ግንብ እየሆነ ተገነባ፤ ምሽጉ ዙሪያ ክቡን ካለው አጥር ሌላ ከግንቡ 30 ሜትር ያህል ራቅ ብሎ በጣም የሾሉ እንጨቶች በምሽጉ ዙሪያ በብዛት ተተከሉ፤ ካንዱ ሹል እንጨት እስከ አንዱ ሹል እንጨት ያለው ርቀትም 20 ሳንቲ ሜትር ያህል ነበር፤ እነኚህ ሹል እንጨቶች ከመሬት በላይ ያላቸው ከፍታ 30 ሳንቲ ሜትር ነው፤ ከሹል እንጨቶቹ አልፎ ደግሞ እሾካማ ሽቦ እየተድቦለቦለ በምሽጉ ዙሪያ እየተተከለ ተከምሯል፤ ከሽቦው ውጭ ደግሞ ጠርሙስ እየተሰበረ እንዲነሰነስ ተደረገ" ይላል።

አፄ ምኒልክ ጦራቸው መቐለ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣሊያን ምሽግ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበት እና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ደንብሮ ወደ ጣሊያኖች ምሽግ ሮጠ። ጣሊያኖችም አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ተኩስ ጀመሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ጣሊያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን በተመለከቱ ጊዜ ራስ አባተ ቧ ያለውን እና ደጃዝማች ባልቻ አባ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዝዘው የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ።

ወደ ማታ ንጉሱ እንደገና ራስ አባተን እና ደጃዝማች ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣሊያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም፤ እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ከዚያ ሆናችሁ ምሽጉን በመድፍ ምቱት” ብለው አዘዟቸው።

ራስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣሊያኖችን ቃፊር (ጠባቂ) አባርረው፣ ምሽግ አበጅተው፣ መድፍና መትረየሳቸውን እንዳጠመዱ ደጃዝማች ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሰርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣሊያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበዙ። አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ራስ አባተም በሩቅ ማሳያ መነጽራቸው ተመልክተው አነጣጥረው ሲተኩሱ የመድፉ ጥይት የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣሊያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ ሲወጣ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ራስ አባተን እና ደጃዝማች ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እሩምታ አወረዱባቸው። ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም አፄ ምኒልክ፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከፍተኛ ስፍራ ላይ ሆነው በመነጽር ሲመለከቱ ነበር።

እቴጌ ጣይቱም ሁኔታውን ሲመለከቱ ስለነበር በአቅራቢያቸው ወደ ነበሩት አዛዥ ዘአማኑኤል ፊታቸውን አዙረው፥ “ሂድ እና ከራስ አባተ ጋር እየተመካከርክ የውኃውን ምንጭ ለመያዝ ትችል እንደሆነ ሞክር” በማለት አዘዟቸው። እሳቸውም ወዲያው በመሄድ እንደታዘዙት ራስ አባተ ጋር ሲነጋገሩ ሊቀ መኳስ አባተ “የምንጩ ስፍራ ጥልቅ እና ወደ ጠላት ምሽግ የቀረበ ነው፤ በምንጩ እና በጠላት ምሽግ መካከል አንድ መቶ ሃምሳ ክንድ የሚሆን ርቀት አለ፤ ቢሆንም ግን መተላለፊያውን በመድፍ ሳስጠብቅ እቆይና ከዚያ በሌሊት ወታደር ልኬ ምንጩን አስይዛለሁ” ብለው መለሱላቸው።

አዛዥ ዘአማኑኤልም ራስ አባተ ያሉትን ለእቴጌ ጣይቱ ሲነግሯቸው በጣም ደስ ስላላቸው፥ “ጠላት ውኃ እንዳይቀዳ ምንጩን ጠብቁ፤ እናንተም እስካሁን ምሽግ ገብተን እንዋጋለን የምትሉት የሜዳን ጦርነት እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ፤ በዚህ ጦርነት ተዋግተው ለተረፉት ደስ የሚያሰኝ የክብር ሽልማት እሰጣቸዋለሁ፤ ለሞቱትም ተዝካራቸውን አወጣለሁ፤ ልጆቻቸውንም አሳድጋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለው ወደ እነ ራስ አባተ ላኳቸው።

ኢትዮጵያውያኑ የጦር መሳሪያቸውን በደንብ አዘጋጅተው፣ እንደተቆጣ ነብር መስለው ወደ ምንጩ ተጉዘው ተቆጣጠሩት። ጣሊያኖቹ ምንጩ ወደ እነሱ ምሽግ በመቅረቡ ይያዛል ብለው አላሰቡም ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው በገባቸው ጊዜ ምንጩን በሚጠብቁት ኢትዮጵያውያን ላይ ድንገት ተኩስ ከፈቱባቸው፤ ጠባቂዎቹም ጠንክረው በመዋጋታቸው ጣሊያኖቹ ወደመጡበት መመለስ ግድ ሆነባቸው።

በማግስቱ ራስ አባተ ከደጃዝማች ባልቻ ጋር ተስማምተው ጣሊያኖቹ ያሉበትን እና መድፋቸውን የጠመዱበትን ቦታ በመነጽር ተመልክተው በመድፍ መቱት። ጣሊያኖቹም ዕቃቸውን መድፍ ወደማይደርስበት አዛወሩ። ሊቀ መኳስ አባተ እና በጅሮንድ ባልቻ በምሽግ ያሉትን በጥብቅ እየጠበቁ ወዲያና ወዲህ እየተዘዋወሩ በመድፍ እና በመትረየስ እየመቱ ጠላት ምሽጉን እስኪለቅ ድረስ ለአሥር ቀን ድረስ ሳይተኙ እና ከመሳሪያቸው ሳይለዩ ሰነበቱ።

እቴጌ ጣይቱም በየቀኑ ከሌሊቱ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውኃውን ለሚጠብቁ ወታደሮች መጠጥ የያዘ እንሥራ እና በመሶብ እንጀራ ሥጋ እየጨመሩ ይልኩ ነበር። በሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለው እና በበጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎ የሚመሩት የጦር ወታደሮችም እየበሉ፣ እየጠጡ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ለመሰዋት ሲሉ አንድ ቀንም መሳሪያቸውን ትተው ሳይተኙ ጠላት ውኃ እንዳይወስድ አድርገው ቆይተው በመጨረሻ ምሽጉን እንዳስለቀቁ ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል።

ራስ አባተ በአምባላጌ ጦርነት በመድፍ የወራሪውን ጦር አርበድብደዋል፤ ከአስደናቂው የአምባላጌ ጦርነት ድል ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በተዋደቁበት የመቐለው የእንዳ ኢየሱስ ጦርነት ላይም በመድፋቸው ገብተውበት የጠላትን ህልም አምክነዋል። የእንዳ ኢየሱስን ምንጭ በመክበብ፣ የወራሪዎችን መድፎች አመድ በማድረግ ጣሊያንን ከመቐለው ምሽግ በማስለቀቁ ጦርነት ታላቅ ባለውለታ ከሚባሉት የጦር መሪዎች መካከል ራስ አባተ አንዱ እና ዋነኛው ነበሩ።

ራስ አባተ ከጠላት ላይ በተማረከው መድፍ ተኩሰው በጠላት መድፍ አፍ ውስጥ አስገብተው የጠላት መድፍ ተኩሱን እንዲያቋርጥ እና አካባቢው ላይ እሳት እንዲነሳ ያደረጉ ጀግና ናቸው።

ለዚህ ጀግንነታቸውም፡-

"ወንጌል ተምሯል ወይ ያባተ ፈረስ፣

ይትረፍ ለነገ አይል ምንም ቢደገስ፤

አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ ሰው፣

ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው፤

አበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ፣

አይነ ጥሩው ተኳሽ ቧ ያለው አባተ" ተብሎ ተገጥሞላቸዋል።

ከድሉ በኋላም ምርኮኛውን እንዲነዱ እና ምርኮውን እንዲያስጫኑ በአጼ ምኒልክ በታዘዙት መሰረት አዲስ አበባ ድረስ ምርኮውን እና ምርኮኛውን ይዘው የሄዱ አርበኛ ነበሩ።

ራስ አባተ፥ አባ ይትረፍ ከተባለው ፈረሳቸው ጋር በጽናት የተዋጉበት ዓድዋ፣ መድፍ ከመድፍ ያቆላለፉበት ሶሎዳ ተራራ፣ በቅኝ ግዛት ስር ለወደቁ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ጮራ እንዲሁም የተስፋ ቀንዲል እና ምስክር ሆነው ይኖራሉ።

ራስ አባተ ጥር 6 ቀን 1910 ዓ.ም በተፈጥሮ ሕመም በ45 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም አርፈው ቀብራቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈፀመ። አባ ይትረፍ ከዚህ ዓለም ቢያልፉም ስማቸው ግን ከታላቁ ተግባራቸው ጋር ዛሬም ድረስ ሕያው ሆኖ ይኖራል።

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top