ስለችሎታ እና ክልከላ ሕጉ ምን ይላል?

5 Mons Ago
ስለችሎታ እና ክልከላ ሕጉ ምን ይላል?

ሁላችንም ሰው በመሆናችን መብት እና ግዴታዎችን የሚፈጥሩ ተግባራትን መከወን እንችላለን።መብት እና ግዴታን የሚፈጥሩ ተግባራት የሚባሉት ውል መዋዋል ፣ወኪል መሆን፣መክሰስ፣መከሰስ፣ንብረት ማፍራት በንብረት መብት መጠቀም፣ ጋብቻ መፈፀም ኑዛዜ ማድረግ እና የመሳሰሉት ናቸው።እነኚህን መብቶችን ለመጠቀም ነፃ እና ምክንያታዊ ውሳኔ መወሰን የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንዳለን ሕግ ግምት ሲወስድ ከእነኚህ ሕጋዊ ውጤት ካላቸው ተግባራት ልንከለከል እንችላለን። እስኪ የፍትሐብሔር ሕጋችን ስለ ክልከላ ምን እንደሚል እንመልከት።

  1. ስለችሎታ

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 192 ‘ሁላችንም በሕግ ተወስኖ ካልተገለፀ በቀር ማንኛውንም አይነት የማህበራዊ ኑሯችንን ተግባር ለመፈፀም ችሎታ አለን’ ይላል። ይህን ችሎታ የሚያሳጡት በዕድሜ ለአካለ መጠን አለመድረስ (ከ18 ዓመት በታች መሆን) የአዕምሮ ህመም፣ድርጊቱን ለመፈፀም ወሳኝ የሆነ የአካል ክፍል ጉዳት እና በፍርድ ቤት የሚጣል ከመብት የመሻር ቅጣት ናቸው፡፡

 የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ የማድረግ ችሎታ የሚያሳጣው ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጋ አለመሆን ሲሆን፤ ለዜጎች ብቻ በተከለሉ ተግባራት ለምሳሌ መምረጥ ወይም መመረጥ፣በተወሰኑ የሥራና የንግድ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ በመገናኛ ብዙሀን፣ በብሮድካስት አገልግሎት እና በመሳሰሉት የተወሰኑ መስኮች ለመሰማራት የኢትዮጵያ ዜጋ ያልሆነ ሰው በሀገራችን ሕጎች ስለተከለከለ ለነዚያ ተግባራት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ባለመሆኑ ችሎታ ይጎለዋል፡፡

ከመብት መሻር ደግሞ የወንጀል ጥፋተኝነትን ተከትሎ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛ ቅጣቶች በተጨማሪ አጥፊው ከተወሰኑ ማህበራዊ መብቶች ለተወሰነ ጊዜ እንዲሻር የሚሰጡት ውሳኔ የሚያስከትለው ክልከላ ነው።

በነገራችን ላይ የተፈጥሮ ሰዎች ብቻ ሳንሆን በሕግ እውቅና ያገኙ ሰው ሰራሽ ሰዎች(ድርጅቶች ፣ ማህበራት ተቋማት) ሰው ሰራሽ ሰውነት በሕግ ስላገኙ የመክሰስ፣ የመከሰስ፣ ውል የመዋዋልና ንብረት የማፍራት ችሎታ አላቸው፡፡

  1. የአዕምሮ ጤና እና ለተግባሩ አስፈላጊ የአካል ክፍል ጉዳት

መብት እና ግዴታ የሚፈጥሩብንን ነገሮች ለመፈፀም ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ ፍቃደኝነት ነው፡፡ ፍቃደኝነታችን ትክክለኛ የሚሆነው ደግሞ የምናደርገውን ነገር በምክንያታዊነት የምናመዛዝንበት የአዕምሮ ወይም የአካል ችሎታ ሲኖረን ነው፡፡

ለምሳሌ የአዕምሮ ህመመተኛ የሆነው አቶ እገሌ አንገቱ ላይ የነበረውን 30 ግራም ወርቅ በ30 ብር ልሽጥላችሁ ቢላችሁ ለማመን ይከብዳችኋል አይደል? እውን በጤናው ነው ብላችሁ ትጠራጠራላችሁ። ከዓይነ ስውሩ አቶ እንቶኔ ጋራ ቤቱን ለመከራየት ውሉን አንብባችሁለት ፈርሞላችኋል። የኪራይ ውል አንብባችሁለት የቤት ሽያጭ ውል ላይ ብታስፈርሙትስ? በርግጥም የሚፈርምበትን ውል አንብቦ ዓይቶ ተስማምቶ ፍቃዱን ለመስጠት ችሎታው ነበረው ትላላችሁ?

እነኚህ ጥያቄዎች የሚነሱት በምሳሌ ያነሳናቸው ሰዎች፤ መደበኛው እና ሁላችንም አለን ተብሎ የሚገመተውን የምናደርገውን ነገር አመዛዝኖ የማወቅ ለአዕምሮ ህመምተኛው፤  ለዓይነ ስውሩ ደግሞ በብሬል ካልሆነ በብዕር ወይም በታይፕ የተፃፈ ውልን ይዘቱ ወረቀቱ ላይ የሰፈረው መሆኑን ዓይቶ ለማረጋገጥ የሚያስፈልገው የአዕምሮ ወይም የአካል ክፍል ስለሚጎላቸው ነው።

  1. ችሎታ እና አዕምሮ

 በ1952 ዓ.ም  የወጣው የፍትሐብሔር ሕጋችን እነኚህ ችሎታዎች ሊጎሉ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ያስቀምጣል። በፍ/ብ/ሕ/ቁ 339 መሰረት የአዕምሮ ህመም ያለበት የሚባለው በተፈጥሯዊ በአዕምሮ ውስንነት ፣ በአዕምሮ ጤና መታወክ ወይም በእርጅና( በመጃጀት) የሚሰራው ስራ የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ የማይችል ሰው ሲሆን፤ በአልኮል ወይም በአደንዛዥ እፅ ሱሰኝነት የተያዙና ገንዘብ ያለ አግባብ የሚያባክኑ ሰዎችም በጤናማ አዕምሮ ድርጊታቸውን አመዛዝነው መለየት ስለማይችሉ ሕጉ የአዕምሮ ችግር እንዳለባቸው ይቆጥራቸዋል፡፡

  1. ችሎታ እና የአካል ጉዳት

መናገር፣ መስማት፣ ማየት የተሳናቸው እና ቋሚ በሆነ የአካል ጉዳት ራሳቸውን ችለው ለመተዳደር ወይም ንብረታቸውን ለማስተዳደር ችሎታ የሌላቸው ሰዎችም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 340 መሰረት የአዕምሮ ችግር ላለባቸው ሰዎች በተቀመጡበት የሕግ ጥበቃዎች መታቀፍ ይችላሉ።

  1. የሕጉ ጥበቃ

 ሕጋችን ይህ ችግር ላለባቸው ወገኖቻችን ያስቀመጠው ጥበቃ የተመሰረተው  'ችግሩ በግልፅ የሚታወቅ ነው ወይድ አይደለም?' በሚለው ነጥብ ላይ ነው ፡፡

 የአዕምሮ ህመምን በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 341 የአዕምሮ ህመምተኞች በሆስፒታል፣ በአዕምሮ ህሙማን ማቆያ ወይም በአዕምሯቸው ሁኔታ በአንድ ጤና ተቋም ጥበቃ እየተደረገላቸው አንዳሻቸው መውጣት መግባት ሳይችሉ በቁጥጥር ስር ባሉበት ጊዜ የአዕምሮ ህመሙ ለማንኛውም ሰው ግልጽ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

ከነዚህ ተቋማት ውጭ ላሉት ደግሞ ከሁለት ሺህ የማያንሱ ነዋሪዎች ባሉበት ቀበሌ ክልል ውስጥ በዘመዶቹ ወይም አብረውት በሚኖሩት ሰዎች በአዕምሮው ሁኔታ የተነሳ የሚያስፈልግ ጥበቃ የሚደረግለት ከሆነ እና እንቅስቃሴው በጠባቂዎቹ ከተገደበ በዚያ ክልል ውስጥ የአዕምሮ ህመሙ በግልፅ እንደሚታወቅ ሕጉ ይገምታል፡፡

  የአካል ጉዳትን በተመለከተ ደግሞ ጉዳቱ ግለሰቡ ራሱን ለማስተዳደር እና ንብረቱን ለማስተዳደር የሚያስፈልገውን ችሎታ እንደሚያሳጣው በግልፅ የሚታይ ከሆነ በየትኛውም ስፍራ ቢሆን ያለበት ችግር በግልፅ እንደሚታወቅ ይቆጠራል፡፡

እነኝህ የአዕምሮ ወይም የአካል ችግራቸው በግልፅ የሚታወቅ ሰዎች፤ የሠሯቸውን ሥራዎች ራሳቸው ግለሰቦቹ፣ ወኪሎቻቸው ወይም ወራሾች ሊቃወሙት ይችላሉ። ይህ ማለት በሕግ ፊት ያን ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልገው ችሎታ እንደሌላቸው በግልፅ ይታያል ተብሎ ስለሚገመት በሚያቀርቡት መቃወሚያ  የሸጡት እቃ ይመለሳል የገቡበት የውል ግዴታም ይፈርሳል። ሆኖም ይህ ተግባራዊ የሚሆነው በተዋዋዮች( ችግሩ ባለበት ሰው እና በሌላኛው ተዋዋይ መሀል) እንጂ በሦስተኛ ወገኖች ላይ በቅን ልቡና (ችግሩን ባለማወቅ) ለሚያደርስባቸው ጉዳት ችግሩ ያለበት ሰው ኃላፊ ይሆናል።

 ይህ የአዕምሮ ወይም የአካል ጉድለት ችግራቸው በግልፅ የማይታወቅ ሰዎች ግን ተዋዋዩ ችግሩን ያውቃል ተብሎ ስለማይገመት፤ በአዕምሮ ወይም በአካል ጉድለት ሰበብ የገቡበት የውል ግዴታ ሊሻርላቸው አይችልም። ተዋዋዩ የውሉን መሻር የሚጠይቅ ከሆነም ውሉ በተደረገበት ወቅት ፍቃዱን መስጠት በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደነበር ካላስረዳ ወይም ውሉ ላይ የአዕምሮ ችግሩ መኖሩን የሚያሳውቅ ነገር ከሌለ ውሉን መሻር ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግለት አይችልም፡፡ 

 ከውል ውጭ ባለ ግንኙነት ግን በግልፅ የሚታወቅ ቢሆንም የአዕምሮ ወይም የአካል ጉድለት ያለበት ሰው ለሚያደርሰው ጉዳት ወይም ለሚያገኘው ያልተገባ ጥቅም እንደ ጤነኞች ሁሉ ኃላፊነት እንዳለበት የፍ/ብ/ሕ/ቁ 350 ይደነግጋል፡፡

  1. ክልከላ

በተለይም ችግሩ በግልፅ በማይታወቅባቸው ሁኔታዎች ሕጉ ያስቀመጠው መፍትሄ ክልከላ ወይም ጥበቃን በፍ/ቤት ማስወሰን ነው። ይህም የችግሩን ተጠቂ ብቻ ሳይሆን ከግለሰቡ የሚፈልጉት ጥቅም ወይም መብት ያላቸውን ለምሳሌ የወራሾቹን፣የንብረት ተጋሪዎቹን ጥቅምም ለመጠበቅ የሚደረግ መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁ 351 ይገልፃል፡፡

 የክልከላ ጥያቄውን እራሱ ግለሰቡ፣ ባል ወይም ሚስት፣ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመዶቹ  ወይም ዓቃቢ ሕግ ሊያቀርበው ይችላል። ጥያቄው የቀረበላቸው ዳኞች ክልከላው የግድ አስፈላጊ መሆኑን በአካል ተገኝተው ግለሰቡን ዓይተው ያረጋግጣሉ። አስፈላጊ ሆኖ ካገኙትም ችግሩ የጀመረበትን ጊዜ ጥያቄው ከቀረበላቸው ቀን ሁለት ዓመት ወደ ኋላ ሄዶ የሚቆጠር አድርገው መወሰን ይችላሉ።

  1. የክልከላ ውጤት

የክልከላ ዓላማ ሌሎች ሰዎች ችግሩን አውቀው እንዲጠነቀቁ ነውና በየክልሉ ክልከላ የተደረገባቸው ሰዎች መዝገብ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቀመጣል። ንብረት ነክ ጥቅሞቹን፣ አካላዊ ደህንነቱንና የጤናውን መሻሻል የሚከታተሉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 359 መሰረት ከቅርብ ቤተሰቦቹ  ወይም ከሌሎች ሰዎች መሀል ሞግዚት እና አሳዳሪ ይሾምለታል ፡፡ በተጨማሪም ከቤተዘመድ ጉባኤ ጋር ምክክር እየተደረገ የተከለከለው ሰው በአሳዳሪው ጥበቃ ይደረግለታል።

 የተከለከለውን ሰው ወክሎ የሚያስፈልጉትን ሕጋዊ ተግባሮች ሁሉ ንብረቱን መጠበቅ እና መቆጣጠርን ጨምሮ ሞግዚቱ ይፈፅምለታል።በተጨማሪም የተከለከለው ሰው ከተፈቀደለት ገደብ በላይ ያደረጋቸውን ውሎች ካሉ ሞግዚቱ በፍ/ቤት ውሎቹን በመቃወም እንዲፈርሱ የማድረግ ስልጣን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 374 ተሰጥቶታል፡፡

 ይህ በፍርድ ቤቶች የሚደረግ ክልከላ አስፈላጊነቱ ለተከልካዩ ጥቅሞች እና መብቶች ጥበቃ ለማድረግ ሲሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 378 የክልከላው ምክንያቶች ከቀሩና ተከልክሎ የነበረው ሰው ንብረቱን ለማስተዳደርና ለመምራት የሚችል ከሆነ ውሳኔውን የሰጠው ፍ/ቤት ክልከላው ያነሳለታል። በፍርድ አጥቶት የነበረውን እንደ ማንኛውም ችሎታ ያለው ሰው ሕጋዊ  ተግባራቱን በራሱ የመፈፀም ችሎታንም መልሶ በፍርድ ውሳኔ  ያገኘዋል፡፡

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top