የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን አስመልከቶ የማጠቃለያ ግምገማ አካሄደ

1 Mon Ago
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን አስመልከቶ የማጠቃለያ ግምገማ አካሄደ

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል 37ኛ የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤን አስመልከቶ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት የማጠቃለያ ግምገማ አካሄደ። 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በማጠቃለያ ግምገማው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ፣ 44ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ እና 28ኛው የቀዳማዊ እመቤቶች ጉባኤን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶች እና በርካታ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች የተሳተፉበት ጉባኤ በሰላምና በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል። 

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ግብረ ኃይል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየተመራ ሪፎርም ማካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጣም ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከለውጡ በፊት አብሮ ተቀምጦ ሥራን መገምገም  ሳይሆን አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነት እያሳየ እርስ በርስ ይገፋፋ እንደነበር አንስተው፤  ተቋማቱ  ከሪፎርም በኋላ እንደ አንድ ተቋም ተቀናጅተው አብረው በመስራት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል። 

በ2016 ዓ.ም ትላልቅ ህዝባዊ፣ መንግስታዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በሰላም መጠናቀቃቸው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስችሏል ብለዋል። 

ከታህሳስ ወር ጀምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ልዩ ኦኘሬሽን በማካሄዳችን ቀላል የማይባሉ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር ችለናል ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ይህም ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል። 

አያይዘውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የፀጥታና ደህንነት መዋቀሩ የራሱ መሆኑን አረጋግጦ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እና ለፖሊስ ከቴክኖሎጂ በላይ ዓይን እና ጆሮ ሆኖ እያገለገለ ያለ ህብረተሰብ መሆኑን አንስተው፤ ለተገኘው ከፍተኛ ስኬት ዋናው መሠረት ህዝቡ በመሆኑ በግብ-ኃይሉ እና በራሳቸው ሥም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። 

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ሲሳይ ቶላ፥ ይህ ውጤት የተገኘው መንግስት ተቋማትን ለመገንባት በወሰደው እርምጃ ነው ብለዋል። 

አክለውም የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት ተቋማቱ በትብብር በመስራታችን ያመጣነው ስኬታማ ውጤት ነው ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፥ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶችን ተቀብለን ያለምንም የፀጥታ ችግር ማስተናገድ የቻልነው የፀጥታ አካላት የ24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠታቸው ነው ካሉ በኋላ ለፀጥታ አካላቱ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። 

የሪፐብሊካን ጋርድ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ጀማል አብዱሮ ከድር በበኩላቸው፥ ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መሳካት የፀጥታና ደኅንነት አካላቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በቅንጅት አብረን በመስራታችን የተገኘ አመርቂ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top