በህዝብ ጉዳዮች ላይ ከህዝቡ ጋር በመስራት ለሀገሪቱ ብልፅግና እውን መሆን በቁርጠኝነት ይሰራል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

2 Mons Ago
በህዝብ ጉዳዮች ላይ ከህዝቡ ጋር በመስራት ለሀገሪቱ ብልፅግና እውን መሆን በቁርጠኝነት ይሰራል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

"ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መርህ ቃል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

ህዝባዊ ውይይቱን የመሩት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ለተነሱ ሀሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም፤ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላምና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ አየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ህዝቡም ሰላሙን ለማስጠበቅ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በውይይቱ ወቅት፤ ከአሶሳ አዲስ አበባ ድረስ ያለው መንገድ ከፀጥታ ችግር ነጻ እንዲሆንና የመንገድ መሠረተ ልማቱም በአዲስ መልክ እንዲሠራ መንግስት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአማራ ክልል በኩል የሚከሰቱ ግጭቶችና የመንገድ መዘጋት ችግሮች እንዲፈቱ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኢስሀቅ አብዱልቃድር፤ የልማት የሰላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በህዝባዊ ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች በሶስቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ የሰላም እጦት፣ የመንገድ መዘጋት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር፣ እንድሁም እነዚህ ችግሮች የወለዱት የኑሮ ውድነት በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያስከተለ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

በጀማል አህመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top