የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጄኔራል፡- ራስ አሉላ አባነጋ

2 Mons Ago
የመጀመሪያው አፍሪካዊ ጄኔራል፡- ራስ አሉላ አባነጋ

 

ኢትዮጵያውያን በዓለም መድረክ ሁሉ በነጻነት አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ፣ ማንነታቸው እንዳይበረዝ እና ታሪካቸውን ለዓለም እንዲነግሩ በቀደመው ዘመን ውድ የሕይወት ዋጋ ተከፍሏል። ይህ ዋጋ ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ እና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የአድዋ ድል ነው። በጀግኖች አባቶች ተጋድሎ የተገኘው የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነጻነት ፋና ወጊ ድልን የጻፉት ራይመንድ ጆናስ "በማያቋርጥ የአውሮፓውያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያ ብቻ ነፃነቷን በተሳካ ሁኔታ አስጠብቃ ነበር" ብለውታል።

 

ለዚህ ድል መገኘት መላ ኢትዮጵያውያን በንጉሠ ነገሥቱ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ በሳል አመራር ከምግብ አብሳዮች እስከ አዋጊ የጦር መሪዎች እና ተዋጊ  ወታደሮች ብሎም ፈረሶች ሁሉም የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ‘አድዋ የአንድነት እና የኅብረት ውጤት ነው’ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

በአርዓያ ሰብ ዝግጅታችን ለአድዋ ድል መገኘት ብቁ ወታደራዊ አመራር በመስጠት እና ጠላትን ፊት ለፊት በመፋለም አንጻባራቂ ድል ያስመዘገቡ ምርጥ የጦር መሪዎችን እንዘክራለን፡፡ ይህም የካቲት ወር ለኢትዮጵያውያን የነጻነት ዓርማ ስለሆነ  የዓድዋ ጀግኖችን በዝግጅታችን እናስባለን፡፡

 

በዛሬው ዝግጅታችን በፈረስ ስማቸው ራስ "አሉላ አባ ነጋ" በትውልድ ስማቸው አሉላ እንግዳ ቁቢን እንመለከታለን፡፡ አሉላ አባ ነጋን የጦር መሪ፣ ሀገር አቅኚ፣ ዲፕሎማት፣ የደህንነት ሰው፣ አርቆ አሳቢ ጀግና የሚሉት ቅጽሎች ብቻ አይገልጿቸውም፡፡ ከኩፊት ጀምሮ እስከ አድዋ ድረስ ነበልባል ክንዳቸውን የቀመሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች የእርሳቸውን ማንነት ይመሰክራሉ፡፡

ራስ አሉላ የተወለዱት በተምቤን ሲሆን አባታቸው እንግዳ ቁቢ ይባላሉ። ራስ አሉላ አመራርን በተፈጥሮ የተቸሩ መሆናቸውን እስራኤላዊው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤርሊች "የራስ አሉላ ታሪክ በመላው ትግራይ የታወቀ ነው፤ በልጅነታቸው ልጆችን እንደ ወታደር ሰብስበው እየመሩ ወደ ሰርግ ቤት የሚሄዱ ሰዎችን አስቁመው ወደ የት እንደሚሄዱ ይጠይቋቸው ነበር" ብለዋል። ሰዎችም "ወዲ ቁቢ ‘ቤተመንግሥቴ ነው’ ብለው በሰፈሩበት የእቃ እቃ ጨዋታ ቦታ እየሄዱ ‘ራስ አሉላ’ በሚል ቅጽል ስም ይጠሯቸው ነበር ይላሉ የታሪክ ጸሐፊው።

አሉላ የእንደርታ ባላባት ለነበሩት ራስ አርዓያ ድምጹ አገልጋይ በመሆን ውትድርናን እንደተማሩ ታሪካቸው ያሳያል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የደጃዝማች ካሳ ምርጫ (የወደፊቱ አፄ ዮሐንስ አራተኛ) አጎት የሆኑትን ራስ አርዓያን ትኩረት መያዝ ቻሉ፡፡ ራስ አርዓያም የአሉላን ታታሪነት እና ታማኝነት በማየት የእልፍኝ አስከልካያቸው አደረጓቸው። ኤርሊች እንደጻፉት አፄ ዮሐንስ ከተቀናቃኛቸው ንጉሥ ተክለጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጦርነት ወጣቱ አሉላ ንጉስ ተክለ ጊዮርጊስን በመማረክ የመጀመሪያ የጦር ሜዳ ጀብዷቸውን አስመዘገቡ፡፡ አሉላ በወቅቱ አባባል ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከነበረው (ጭሰኛ) ቤተሰብ ቢወጡም በታማኝነታቸው እና በጀግንነታቸው የመሳፍንት እና የነገሥታት ዘሮች ብቻ በሚያገኙት ከፍተኛ የሥልጣን ተዋረድ መሰላል ላይ በፍጥነት ሊወጡ ችለዋል።

 

በ1867 እና በ1868 በተካሄዱት የጉንደት እና ጉራዕ ጦርነቶች ለውጭ ወራሪዎች የሚፋጅ ክንዳቸውን በማሳየት ወታደራዊ ክህሎታቸውን ማሳየት ጀመሩ። በነዚያ ጦርነቶች ወራሪውን የግብፅ ጦር አንኮታኮቱት። አፄ ዮሐንስ በሃማሴን አመጽ የቀሰቀሱትን ራስ ወልደ ሚካኤል ሰለሞንን ለማስታገስ ይህን ልዩ ክህሎት ያለው ወጣት ፈለጉት፤ አሉላን ራስ ብለው ሾመው ወደ ቦጎስ የሸሹትን ራስ ወልደ ሚካኤልን እንዲይዙ ላኩት። ራስ አሉላም ተልዕኳቸውን በስኬት አጠናቀው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ግርማ ሞገስን አገኙ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ራስ አሉላን የመረብ ምላሽ እና የምድሪ ባሕሪ (የዛሬው የኤርትራ) አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸው። 

 

የራስ አሉላ የጦር ሜዳ ውሎዎች ሁሉ የድል እና የስኬት ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየቀጡ ወደ ግዙፉ እና ታሪክ ቀያሪው የአድዋ ድል ያመሩት ወዲ ቁቢ ከአድዋ በፊት ከግብፅ፣ ከመሃዲስት (የሱዳን) እና ጣሊያን ጋር ሦስት ታላላቅ ፍልሚያዎችን አድርገው ለወራሪዎቹ ነበልባል ክንዳቸውን አቅምሰዋቸዋል፡፡ እነዚህ የጦር ሜዳ ውሎዎቻቸውም፡-

  1. የኩፊት ጦርነት

ራስ አሉላ አገዛዛቸውን ያልተቀበሉ አንዳንድ የአካባቢው መሪዎችን ጭምር ተቃውሞ እየገጠማቸው ማህዲስቶችን ለመውጋት ተዘጋጁ። አሉላ ወደ ቦጎስ ከገቡ በኋላ ወደ ከረን ሄዱ፤ በዚያም ለአሥር ቀናት ከቆዩ በኋላ ወደ ኩፊት ዘምተዋል።

በኩፊት ከሱዳን ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊወር የተንቀሳቀሰው የኡስማን ዲግና ሠራዊት በራስ አሉላ ሠራዊት ተደምስሷል። በዚህ ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል የአሉላ ሠራዊት አዛዦቹ ብላታ ገብሩ እና አጋፋሪ ሃጎስ ሕይወታቸው አልፎ ራስ አሉላም ቆስለው የነበረ ቢሆንም ድላቸውን ከማረጋገጥ አላገዳቸውም።  

  1. የዶጋሊ ጦርነት

ራስ አሉላ ጣሊያኖች በምፅዋ በኩል ወደ ውስጥ እየተስፋፉ መሆናቸውን ሲያስተውሉ፣ ወራሪዎቹ ግዛታችንን ለቀው ካልወጡ እንደሚያጠፏቸው ለጣሊያን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ባለሥልጣናት ጻፉ። ይሁን እንጂ ጣሊያኖች "ጣሊያን ወደ ምፅዋ የመጣችው በመለኮታዊ ፈቃድ" እንደሆነ በማሳወቅ ለራስ አሉላ ጥያቄ በምጸት የተሞላ ምላሽ ሰጡ።

በዚህም ከጣሊያን ጋር ወደ ግጭት መገባቱ አይቀሬ መሆኑን የተረዱት ራስ አሉላ ጦራቸውን አሰባስበው ዝግጅት ጀመሩ፡፡ የመጀመሪያው ግጭት የተካሄደው ታኅሳስ 1888 በሰአጢ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ራስ አሉላ እንደገና ወታደሮቻቸውን አሰባስበው ጣሊያንን በዶጋሊ ገጥመው ድባቅ መቷቸው። በጦርነቱም የጣሊያኑ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ቶማሶ ደ ክሪስቶፎሪስ ከ400 ወታደሮች እና ከ22 መኮንኖች ጋር በዚህ ውጊያ ተደምስሰዋል።  

  1. የገለባት ጦርነት

ሱዳን ማህዲስቶች፣ ጣሊያኖች እና ደርቡሾች ኢትዮጵያን ለማጥቃት መዘጋጀታቸውን ራስ አሉላ መረጃ ደረሳቸው። በገለባት (መተማ) ጦርነት አጼ ዮሐንስ በጦርነቱ ላይ የሞቱ ሲሆን፣ ራስ አሉላ እንደገና ጦራቸውን አደራጅተው የጠላትን ጦር ወደ መጣበት መለሱት፡፡

የንጉሠ ነገሥቱን ሞት ተከትሎ በአጼ ምኒሊክ እና በአጼ ዮሐንስ አራተኛ አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ መንገሻ መካከል የተፈጠረውን የሥልጣን ሽኩቻ በመጠቀም ጣሊያን ኤርትራ ቅኝ ግዛቷ መሆኑን አወጀች፡፡ "ፈረሴን ከቀይ ባሕር ሳላጠጣ እረፍት የለኝም” ሲሉ የነበሩት ራስ አሉላ ትልቅ ፈተና ፊታቸው ተደቀነ፡፡

 

በዚህ መካከል የተወጠሩት እና በሁለቱ ወገኖች መካከል በተፈጠረው ሽኩቻ ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑን የተረዱት ራስ አሉላ፤ ልዑል ራስ መንገሻን ወደ ሸዋ ይዘው መጥተው ከአጼ ምኒልክ ጋር በማስማማት ለቀጣዩ ፈተና መዘጋጀት ጀመሩ፡፡

 

የአድዋ ድል፦ ደማቁ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ችቦ

የውጫሌን ስምምነት ተከትሎ ጣሊያኖች በአጎርዳት ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በአድዋ ዙሪያም ወደ ምዕራብ መስፋፋታቸውን ቀጠሉ። አፄ ምኒልክ ያላወቁት የውጫሌ ስምምነት የጣልያንኛው ትርጉም ጣሊያንን የኢትዮጵያ ጠባቂ የሚያደርጋት ነበረ። ጣልያኖችም ግዛት ማስፋፋቱን ቀጠሉ። አፄ ምኒልክ ይህን ክህደት ባወቁ ጊዜ ውሉን መሰረዛቸውን አሳወቁ። ራስ አሉላን ጨምሮ ዋና ዋናዎቹ መኳንንት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት በአንድ ድምጽ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ለመውጋት ዝግጅት ጀመሩ። ጦርነቱም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ረፋድ ላይ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ።

በዚህ ውጊያ ላይ የራስ አሉላ፣ የራስ መኮንን እና የራስ ሚካኤል ጦሮችን በማጣመር ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ከሚመሩት ጦር በስተግራ በኩል ተሰልፈው በአዲ አቡኔ ከፍታዎች ላይ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል አንኮታኮቱ። የአጋሜው የደጃዝማች ሀጎስ ተፈሪ ኃይሎችም የራስ አሉላ እና ራስ መንገሻን ጦሮች ተቀላቅለው ድሉን አጀቡት።

ራስ አሉላ ጣሊያኑን ጦር መሪ ጋስጎሪ እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ እና የጣሊያን ደጀን ከአዲ ኳላ ግንባር ላለው ጦር እንዳይደርስ እንዲከለክሉ እና እንዲያጠቁ ተመደቡ። ጀግናውም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በትክክል በመወጣት ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ያበራችው የነጻነት ችቦ እንድትለኮስ የድርሻቸውን ተወጡ፡፡

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top