ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ኢፍትሃዊው ዓለም የዘጋብንን በር መክፈት እንችላለን

8 Mons Ago 2365
ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ኢፍትሃዊው ዓለም የዘጋብንን በር መክፈት እንችላለን

ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት በላይ የባሕር በር ተዘግቶባት ቆይታለች። በባሕር በርን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ሲያነሱም ቆይተዋል። ጥያቄው የፍትሕ ጥየቄ ቢሆንም ከለውጡ በፊት በነበረው መንግሥት ዳተኝነት እና በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ምክንያት ተዳፍኖ ቆይቷል።

ጥያቄው የትውልድ በመሆኑ ግን አሁን ገፍቶ መጥቶ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደምትፈልግ በይፋ ገልጻለች። ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምትፈልገው ግን በማንኛውም ሁኔታ የሌሎችን መብት በመጋፋት እና በጦርነት ሳይሆን ሰጥቶ በመቀበል እና ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መንገድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጻለች። ይህን ፍላጎቷን ደጋግማ ብትገልጽም ግን ብዙዎች እሷ ያላለችውን በመተንበይ የሀገራትን ስም እየጠሩ ጦርነት ልትከፍትባቸው ነው እየተባለ ቆይቷል። በተለይም ቀይ ባሕር ሲባል ከኤርትራ ጋር ብቻ በማያያዝ የሁለቱን ሀገራት ወደ ጦርነት መግባት የቋመጡ ወገኖች የጦርነት ነጋሪት ሲመቱ ከርመዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ፍላጎቷ መተንፈሻ ማግኘት እንጂ ማን ላይ ጦር የመስበቅ ዓላማ አለመሆኑን የሚመሰክር የመግባቢያ ሰምምነት ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማለች። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ጥያቄ ሌላ የራሳቸውን ሲሰጡ የነበሩ ወገኖች አሁን ደግሞ ሌላ ትርጉም በመስጠት ተቃውሞአቸውን ቀጥለዋል። ሶማሊላንድ ሕጋዊ ሀገር ስላልሆነች ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መፈጸም አትችልም ከሚሉት አንስቶ ኢትዮጵያ የሶማሌን ሉዓላዊነት ስለጣሰች እኛ ከሶማሌ ጎን እንሰለፋለን የሚሉ የሀገር ልጆችን ሁሉ ለማየት ችለናል።

ሶማሊላንድ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት ስትፈርም ዝምታን የመረጡ የጎረቤትም ሆነ የሩቅ ሀገራት ኢትዮጵያ የሶማሌን ሉዓላዊነት በመዳፈር ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሳለች በማለት ከሶማሌ ጎን እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት የጣሰ ነው? ሶማሊላንድስ ይህን ሰምምነት መፈረም አትችልም? የሀገርነት ዕውቅና ለማግኘትስ ምን ጎደላት? አፍሪካ ኅብረትስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሰራ? በዛሬው ሳይበር ዓለም አቀፍ ዝግጅታችን እነዚህን ጉዳዮች እንዳስሳለን።

የሶማሊላንድ አጠቃላይ ሁኔታ 

እ.አ.አ በ2021 በተደረገ ጥናት የሶማሊላንድ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 3.34 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፣ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 775 ዶላር ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የሶማሊያ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 7.628 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 446.98 ዶላር ነበር፡፡ በወቅቱ የሶማሊላንድ ሕዝብ ብዛት 5.7 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ የሶማሊያ ደግሞ 13.3 ሚሊዮን ተገምቶ ነበር፡፡ 

እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የተረጋጋ መንግሥት የመሰረተችው ሶማሊላንድ በኢኮኖሚ ከሶማሊያ እግጅ የተሻለች አንደሆነ ነው። ይህ የሶማሊላንድ አንጻራዊ ብልፅግና የበለጠ ወደ ሉዓላዊነት እንደሚያመራት እና በሶማሊያ መንግሥት ላይ ትልቅ ፈተና ሆኖ እንደቆየ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የንግድ ልማት ባለሙያ የሆኑት ቶማስ ጆኤል ኪብዋና (@thomasjkibwana) ይገልጻሉ። 

ስለ ሉዓላዊ መንግሥትነት ዓለም አቀፍ ስምምነት 

በ1933 ዓም የተፈረመው የሞንተቪዶ ስምምነት አንቀጽ አንድ እንደ አንድ አካል ዕወቅና ያለው መንግሥትነትን ሲተረጉም፣ የታወቀ የግዛት ክልል፣ በግዛቱ በቋሚነት የሚኖር ሕዝብ፣ ግዛቱን በአግባቡ የሚቆጣጠር ወይም የሚያስተዳድር እና ዓለም-አቀፍ ግንኙነቶችን ማድረግ የሚችል መንግሥት ያለው ይለዋል። 

ከዚህ አንጻር ሶማሊላንድ አብዛኛዎቹን መመዝኛዎች ካሟላች ሦስት አስርተ ዓመታት አልፏታል። ይህን እውነታ ስንመለከት የሶማሊያ ሉዓላዊ አንድነት የተናጋው አሁን ሶማሊላንድ ከኢትዮጰያ ጋር ውል ስለፈረመች ሳይሆን ቀድሞውንም በአልሸባብ እየታመሰ ባለው ቀጠና ውስጥ አምስት የተረጋጉ ምርጫዎችን አካሂዳ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ስታደርግ ነው። 

በዚሁ ስምምነት አንቀጽ ሦስት ላይ፣ “ለአንድ ግዛት ፖለቲካዊ ዕውቅና መስጠትም ሆነ መከልከል የሌላ ሀገር ውሳኔ ሳይሆን ግዛቱ ራሱ የሚወስነው ነው፣ ይህን መብት ለማግኘት ምንም ዓይነት የውጭ ተፅኖ አይከለክልም” ይላል። በመሆኑም ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የረጅም ጊዜ ጥቅማቸውን ግምት ውስጥ አስገብተው የፈጸሙት ውል የሚወሰነው በተፈራራሚዎቹ አካላት እንጂ በሌላ ሀገር ፈቃድ አይደለም። 

የተደበቀው የአፍሪካ ኅብረት ጥናት 

በአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር ፓትሪክ ማዚማካ የተመራ እና የኅብረቱ ወታደራዊ፣ ሰላም እና ደኅንነት፣ የስደተኞች እና ሰብዓዊ ጉዳዮች እና የፖሊስ ጉዳዮች ዲፓርትመንት ከፍተኛ ባለሙያዎችን ያካተተ የሶማሊላንድ እውነታ አፈላላጊ ቡድን (AU Fact-Finding Mission to Somaliland) እ.አ.አ ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2005 በሶማሊላንድ ቆይቶ ሰለ ግዛቷ ሁኔታ ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ 

ቡድኑ በሶማሊላንድ ባደረገው ቆይታ ከግዛቷ ፖለቲካ ተወካዮች፣ ከሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፣ ከመንግሥት ካቢኔ አባላት፣ ከፓርላማ አባላት፣ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሶማሊላንድ ሉዓላዊነት ጥያቄ መልዕክተኛ፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና የሴቶቸ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ የበርበራ ወደብን፣ በማዕከላዊ ሶማሊላንድ የምትገኘውን ሼይክ ከተማ፣ በደቡባዊ ክልል የምትገኘውን ቡራኦ ከተማ እና በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የምትገኘውን ቦራማ ከተማን ጎብኝቷል፡፡ ቡድኑ በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሕዝቡ ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸው በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የዚህ ቡድን ጥናት ግኝትም የሶማሊላንድ ሕዝብ ግዛቲቱ ሉዓላዊ ሀገር እንደሆነች እንደሚያምን ያሳያል፡፡ በተለይም በሕዝቡ ዘንድ ዝነኛ አባባል ነው ተብሎ በሪፖርቱ የተጠቀሰው፣ "ከእንግዲህ ሞቃዲሾ የለችም፤ ከእንግዲህ ሶማሊያ የለችም፤ ሶማሊላንድ ነጻ ሀገር ናት፤ ዕውቅና እንፈልጋለን፤ ይህ መብታችን ነው" (“No more Mogadishu; No more Somalia; Somaliland is Independent Country; we want recognition; it is our right”) የሚለው ነው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ለነጻነቱ ያለውን ቁርጠኝነት ቡድኑ መረዳቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ሶማሊላንድ በ1960 ከሶማሊያ ጋር ተዋህዳ የነበረ ቢሆንም፣ የዚያድ ባሬ መንግሥት እ.አ.አ በ1991 ከፈረሰ እና ሶማሊያ መንግሥት አልባ ከሆነች በኋላ ሶማሊላንድ በእንግሊዝ ስትገዛ በነበረበት ወቅት የነበረውን የቅኝ ግዛት ድንበር ይዛ ለሀገርነት የሚያበቁአትን ተከታታይ ሥራዎች ስትሠራ እንደቆየች ጥናቱ አመልክቷል፡፡ 

ሶማሊላንድ ሕገ-መንግሥት እንዳላትም ተጠቅሷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የመንግሥቷን የሥልጣን ክፍፍል እና አጠቃላይ ሁኔታዎችን የያዘ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ አንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ‘የሀገሪቱን ሉዓላዊ ድንበር የሚከላከል የጦር ሠራዊት’ እንዳላትም ተገልጿል፡፡ 

ሀገር በቀል ውይይቶችን በማድረግ በትጥቅ ማስፈታት፣ ታጣቂዎችን በመበተን እና መልሶ በማቋቋም ከጎረቤቷ ሞቃዲሾ የተሻለች ሰላማዊት ግዛት ሆና እንደቆየች ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በየብስ እና ባሕር ሀብቶቿ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ምጣኔ ሀብት እንዳላትም ተመላክቷል፡፡ 

በሪፖርቱ ማጠቃለያም እ.አ.አ በ1960 ከሶማሊያ ጋር የተደረገው ውህደት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊነትን እና ስቃይን ያስከተለ እንዲሁም ሕጋዊነቱ ያልተረጋገጠ እንደነበረ ተጠቅሷል፡፡ ይህም የሶማሊላንድ ሕዝብ የራሱን ሀገር የመመሥረት ፍላጎቱ ከፍተኛ እንዲሆን እንዳደረገው እና አሁን ያለችው ሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እንድትፈጠር እንዳደረገ ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ይህን ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲሄድበት ምክረ-ሀሳብ አስቀምጧል፡፡      

የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊላንድን ሕዝብ የሉዓላዊነት ፍላጎት ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ከታሪካዊ ዳራዎች አንጻር በመመልከት መፍተሔ ሊሰጥ እንደሚገባ፣ በሀርጌሳ እና ሞቃዲሾ መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነትም ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመልስ የቡድኑ የማጠቃለያ ምክረ-ሀሳብ ነው፡፡ 

ታዲያ የአፍሪካ ኅብረት ይህን መሬት ወርዶ ትክክለኛ የሶማሊላንድን ሕዝብ ፍላጎት ያንጸባረቀ የጥናት ውጤት ይዞ ለምን ተግባራዊ እንቅስቃሴ አላደረገም? ይህ ኅበረቱ ብቻ ምክንያቱን የሚያውቀው እና የሚመልሰው ጥያቄ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣ ሞሪሽየስ እና ቡሩንዲ በአሜሪካ ኤምባሲ ረዳት መልዕተኛነት፣ እ.አ.አ ከ1991 ጀምሮ ደግሞ በሶማሊያ የመጀመሪያው የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን ያገለገሉት እና ከ2017 ጀምሮ የከፍተኛ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት አባልና የሚኒስትር አማካሪ በመሆን ያገለገሉት አምባሳደር ስቲቨን ማይክል ሽዋርትዝ “Foreign Policy Research Institute” ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የአፍሪካ ኅብረት ጥናት ወደ ተግባር መለወጥ አለበት ይላሉ፡፡ 

ለዚህም አፍሪካ ኅብረት ጥናቱን ወደ ተግባር የሚለውጥ አዲስ ቡድን በማቋቋም ሁለቱ አካላት ባሉበት ውይይት እንዲያካሂድ፣ ውይይቱ የሚያመጣውን ውጤት እንዲቀበሉ ማግባባት እና ውይይቱን የሚየሰናክል አካል ኃላፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ኅብረቱ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ትልቅ ስህተት እንደሆነ እና ይህም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር እንደሚያደርግ አስጠንቅቀዋል፡፡ 

ሶማሊላንድ ከሀገራት ጋር ያላት ሁለትዮሽ ግንኙነቶች 

የተለያዩ ሀገራት በተለያዩ ደረጃዎች ከሶማሊላንድ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከነዚህ ሀገራት መካከልም፡- ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ፊሊፒንስ እና ቱርክ በቆንስላ ጽ/ቤት፤ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዴንማርክ እና ኬንያ በአገናኝ ቢሮ (Liaison Office) እንዲሁም ታይዋን፣ ግብፅ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት በተወካይ ቢሮ አማካኝነት ከሶማሊላንድ ጋር ቋሚ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የፈጠሩ ሀገራት ናቸው፡፡ 

እንደ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ያሉ ሀገራት ሶማሊላንድ እ.አ.አ በ2017 ያካሄደችውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚታዘቡ ልዑካን ቡድኖችን ልከዋል። 

ሶማሊላንድ ከሌሎች ሀገራት ጋር የተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ሰምምነቶች 

እ.ኤ.አ በየካቲት 2017 ሶማሊላንድ እና የተባበሩት የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት በበርበራ ወደብ ላይ ወታደራዊ ሰፈር እንዲመሰረት እና የበርበራ አውሮፕላን ማረፊያን ለማደስ የተፈራረሙትን ውል የሁለቱም ሀገራት ፓርላማዎች አጽድቀዋል። የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትም በዲፒ ወርልድ አማካኝነት ወደቡን አድሳ የባሕር ኃይሏ እንዲሰፍርበት እድርጋለች፡፡ 

እ.አ.አ በ2020 ኬኒያ እና ሶማሊላንድ በየሀገሮቻቸው ኤምባሲ ለመክፈት እና የኬንያ አየር መንገድ ወደ ሀርጌሳ በረራ እንዲጀምር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ 

እ.አ.አ በ2009 የፓኪስታን መንግሥት የውጭ ጉዳይ መልዕክተኞች ሶማሊላንድን ጎብኝተው በኢስላማባድ የሶማሊላንድ ንግድ ጽ/ቤትን መክፈት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመው ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ 

እ.ኤ.አ በ2007 አሜሪካ ለ2010 የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ አባላት ምርጫ ዝግጅት እና ለሌሎች ቁልፍ ፕሮግራሞች ሥልጠና የሚውል አንድ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ሰጥታለች። 

እ.ኤ.አ በ2020 ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዴንማርክና ኔዘርላንድስ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ እና ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ተቋማትን ለማሻሻል ከሶማሊላንድ መንግሥት ጋር አራት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ 

የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች እና ግዛቶች ሀገራቸው ለሶማሊላንድ የሉዓላዊ መንግሥትነትን ዕውቅና እንድትጥ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያስ ኃጢአት ምንድን ነው? 

ታዲያ ሶማሊላንድ ባለፉት 30 ዓመታት በቆንስላ ደረጃ ከሀገራት ጋር ግንኙነት እያደረገች፣ የተለያዩ ሰምምነቶን እየተፈራረመች ቆይታ አሁን ከኢትዮጵያ ጋር ስትፈራረም ሶማሊያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ለምን ጥያቄ አነሱ? 

የቀይ ባሕር ቀጠና የሆነው ምሥራቅ አፍሪካ የብዙዎች ትኩረት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኃያላኑ በቀጠናው ጎልብቶ አካባቢውን የሚቆጣጠር እና ከነሱ እይታ ውጭ የሚሆን ሀገር አይፈልጉም፡፡ በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር የጥቅም ሽኩቻ ያለባቸው እና ኢትዮጵያ በቀጠናው ተጠናክራ ከወጣች በአካባቢው ላይ የምንፈልገውን ጥቅም ልናገኝ አንችልም የሚሉ እንደ ግብፅ ያሉ ሀገራት በተለያየ መንገድ ጫና ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ 

ለዚህም ጥሩ ማሳያ ኢትዮጵያ ከግዛቷ በሚመነጨው እና ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ በምታበረክትበት ዓባይ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳታከናውን እንደ የዓለም ባንክ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጫና ሲደረግባት ለመቆየቱ ታሪክ ምሥክር ነው፡፡ 

ግብፅ ከኢትዮጵያ ተራሮች መንጭቶ ሀገሯ የሚገባው የአባይ ወንዝ ላይ አስዋን ግድብን ስትገነባ በሁሉም ነገር የተባበረው ዓለም እና ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ኢትዮጵያ ፊቷን ያዞረባትን ዓለም ትታ በራሷ ልጆች ህዳሴ ግድብን ልትገነባ ስትነሳ ያላደረጉባት ጫና አልነበረም፡፡ 

የሕዝቧን ኑሮ ለመለወጥ በልጇቿ ላብ እያታተረች ያለችው ኢትዮጵያ የውሃ ግድብ ሳይሆን ኒውክልየር እየገነባች ያለች ይመስል ፍርደ ገምድሉ የፀጥታው ምክር ቤት በግብፅ አቤቱታ ኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ ሊወስን በተደጋጋሚ ተሰብስቧል፡፡ ታዲያ ይህ አድሎአዊ ዓለም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ስምምነት ስታደርግ ዝም ሊል ኖሯል? 

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ይዞታ እንድታጣ የተደረገው ልጆቿን በመጠቀም በስልት ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ኢትዮጵያ የነበሯትን የምጽዋ እና አሰብ የባሕር በሮች እንድታጣ የተደረገው ከኤርትራ መገንጠል ጋር በተያያዘ ነው፡፡ 

አስገራሚው ነገር ኤርትራ ስትገነጠል ዕወቅና የሰጠው የኢትዮጵያ አስተዳደር የሽግግር አስተዳደር መሆኑ ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት ደግሞ ቋሚ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ ሀገር ውስጥ ያለውን ሰለም አስጠብቆ የሽግግር ጊዜውን የሚያመቻች እንጂ በውጭ ጉዳዮች ላይ የሚወስን አካል አይደለም፡፡ 

ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር) “አሰብ የማን ናት?” በሚለው መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት በታሪክ የትኛውም ሀገር አድርጎት የማያውቀውን የግዛቱ አካል የነበረ አንድ አካል ተገንጥሎ ሉዓላዊ ሀገር እንዲሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ የጻፈው የወቅቱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ያልተሰጠውን ሥልጣን ከመጠቀሙም በላይ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ድጋፍ እንዳላት እንኳን መከራከር ቀርቶ ይህ ጥያቄ መነሳት ነበረበት ባሉት አካላት ላይ ወከባ ሲፈጽም እንደነበረ ጠቅሰዋል፡፡ 

ምን ይደረግ? 

ኢትዮጵያ የባሕር በር አንገብጋቢ ጥያቄዋ ቢሆንም ማግኘት የምትፈልገው ግን በኃይል እና ሌላውን በመግፋት እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጻለች፡፡ በግዛቷ ውስጥ የምትገነባውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እንኳን ስትጀምር የታችኛዎቹን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን ለውይይት አቅርባ ነው፡፡ 

ይህን እውነታ መስማት የማይፈልገው ዓለም ግን ለሕዝቧ ህልውና ስትል የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ሁሉ የተለየ ትርጉም እየሰጠ ሲያዋክባት ይታያል፡፡ ለዚህም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚፈጠሩ ቁርሾዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ታጣቂዎችን ስፖንሰር በማድረግ፣ በውጭ ዓለም ያሉ ባንዳዎች የፕሮፓጋንዳ ጦራቸውን ሀገራቸው ላይ እንዲሰብቁ ጽ/ቤት እና ሚዲያዎችን ከፍቶ በመስጠት የቻሉትን እያደረጉ ኖረዋል፤ አሁንም ኢትዮጵያን ሰላም የሚነሳትን ሁሉ መደገፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

እነዚህ አካላት አንድ ያልተረዱት ነገር የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም መሆኑን ነው፡፡ ወከባው እንዲሁ ከቀጠለ የተዘጋበት ሕዝብ አንድ ቀን ጎርፍ ሆኖ አካባቢውን ማጥለቅለቁ አይቀርም፡፡ 

ኢትዮጵያ ልጆቿ ባይከዱአት እና የታሪካዊ ጠላቶቿ መሣሪያዎች ባይሆኑ አሁን የተጋፈጠችውን ፈተና አትጋፈጥም ነበረ፡፡ አሁን በውጭ ኃይሎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ኢትዮጵያ ላይ ጦር የሰበቁት የእናት ጡት ነካሽ ልጆቿም በሚጽፉት መጥፎ ታሪክ ነገ የልጅ ልጆቻቸው እንደሚያፍሩባቸው ጥርጥር የለውም፡፡ 

እናም የቤታችንን አመል በቤታችን አድርገን፣ ልብ ገዝተን በመተባበር የሚገባንን እንጠይቅ፤ ኢትዮጵያንም ወደ ክብር ማማዋ እንመልስ መልዕክታችን ነው፡፡ 

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top