የበዓላት ሰሞን አመጋገብ ምን መምሰል አለበት?

6 Mons Ago
የበዓላት ሰሞን አመጋገብ ምን መምሰል አለበት?

በነገው ዕለት በክርስትና ዕምነት ተከትዮች ዘንድ የገና በዓል በድምቀት ይከበራል፡፡ በመሆኑም ከረዥም ጊዜ ጾም በኋላ በዓላትን ተከትሎ በርካቶች ከወትሮው የተለዩ የምግብና መጠጥ ዓይነቶችን የሚጠቀሙበት አጋጣሚ የበዛ ይሆናል።

በዚህም የአመጋገብ ጥንቃቄ ባለማድረግ ብቻ የጤና መቃወስ የሚገጥማቸው ሰዎች መኖራቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።በበዓላት ወቅት የምንከተለው ያልተገባ አመጋገብ ጤና የሚነሳ ወይም ላልተጠበቀ አደጋና እስከ ሕይወት ማለፍ ሊዳርግ እንደሚችልም ይገልጻል።

በተለይም ከመጠን በላይ መመገብ፣ ስጋና የእንስሳት ተዋጽኦን ማዘውተር እንዲሁም የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠጣት የጤና እክል የሚያስከትል ነው።አጽዋማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ፣ የእንስሳት ተዕዋጽዎ ምግቦችን፤ ማለትም:- ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦችን መመገብ እንዲሁም የአልኮል መጠጦችን መጠጣት የተለመደ ነው።

ይህም ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየን ጨጓራ ለህመም የመዳረግ ዕድሉ ከፍተኛ ስለሚሆን፤ የሆድ መነፋት፣ የሆድ ቁርጠት፣ የጨጓራ ማቃጠል ህመሞችን ሊያስከትል ይችላል። ይህም ጥንቃቄ ካልተደረገ ላልተጠበቀ የጤና ችግር የሚዳርግ ሊሆን ይችላል።

ታድያ ይህን ለማስቀረት በበዓላት ወቅት እነዚህ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ:-

*የተለያዩ ምግቦችንና መጠጦችን በአንድ ላይ ቀላቅሎ አለመመገብ።

*የምናዘጋጀው ምግብ ንጽህናን በጠበቀ መልኩ ማዘጋጀት።

*ምግቦቻችን ቅባት የበዛባቸው እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ።

*ስንመገብ ቀስበቀስ ጨጓራን በማላመድ፣ በልክ እና ከመጠን ባላለፈ መልኩ መመገብ

*ጣፋጭ ምግቦችን እና የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ አለመውሰድ

*ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አለመመገብ

አጿዋማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች  ያስረዳሉ። የገና እንዲሁም  የፋሲካ በዓላት በመጡ ቁጥር አንዳንድ ሰዎች ቅባት የበዛበት ምግብ ተመግበው ለሕመም የሚጋለጡበት ሁኔታ ይከሰታል።

ታዲያ በዓልን በሰላም ለማክበር ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች የበዓላት ሰሞን አመጋገብ አንዱና ዋነኛው ስለሆነ፣ ጤናማ የበዓል አመጋገብን በመከተል ጤናን መጠበቅ ያስፈልጋል።  በጤና የታጀበ በዓል ይሁንሎ። መልካም በዓል!!

በሜሮን  ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top