የምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ዘላቂ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የቡሬ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

2 Mons Ago
የምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ዘላቂ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የቡሬ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

የምዕራብ ጎጃም ኮማንድ ፖስት የቡሬ ከተማ ነዋሪዎችን አስተባብሮ የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ሕዝባዊ ውይይት አካሂዷል።

የምዕራብ ጎጃም ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጄነራል መለስ መንግስቴ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ እና የቡሬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምስጋናው ጌትነት በጋራ በመሆን ሕዝባዊ ውይይቱን መርተዋል።

አመራሮቹ ምዕራብ ጎጃም ዞን ትርፍ አምራች አካባቢ በመሆኑ ልማት እና እድገት እንጂ ሁከት እና ብጥብጥ አይመጥነውም ብለዋል።

በመሆኑም ሰላምን ማደፍረስ የሚፈልጉ አካላትን ኅብረተሰቡ በቃ ሊላቸው ይገባል ነው ያሉት።

የዞኑን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የተቋረጠውን ትምህርት እና የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ለማድረግ ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ለሕዝቡ የሚከፍለው ዋጋ እና መስዋዕትነት የሚለካው በሕዝቡ ሰላም እና ኑሮ መሻሻል በመሆኑ፤ አስተማማኝ ሰላም እስከሚረጋገጥ ድረስ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።

የሕዝብ እና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ መከላከያ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እንደሚሠራም አመራሮቹ ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም በትኩረት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

"ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በመከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት ተቀልብሶ የተረጋጋ ቀጣና ተፈጥሮልናል፣ እናመሰግናለን" ሲሉም ነዋሪዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የንግድ ተቋማት እና የገበያ ቦታዎች እንዲከፈቱ፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች አገልግሎት እንዲሰጡ እና የተቋረጠው የመማር ማስተማር ስራ ተመልሶ እንዲጀመር በመወሰኑ መደሰታቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በቀጣይነትም አካባቢው ወደ ዘላቂ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።