የፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመርን ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጀት ስራዎች ላይ ውይይት ተካሄደ

7 Mons Ago
የፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመርን ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጀት ስራዎች ላይ ውይይት ተካሄደ

በበቂ መረጃ የተደገፉ ስራዎችን ማከናወን ለፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመር ማሻሻያ ሂደት ቁልፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሆናቸው ተገለጸ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች የፌዴራል ድጎማ በጀት ቀመርን ለማሻሻል በሚያስችሉ የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችን ጨምሮ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ሀገራዊ ኃላፊነቶች መካከል የክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር መወሰን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ምክር ቤቱም የተጣሉበትን ኃላፊነቶችና የወጡ ሕጎችን ተከትሎ የሕገ መንግሥት የበላይነት፣ ሕገ መንግስታዊነት፣ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ፤ እንዲሁም አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ሀገራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በክልሎች መካከል ውጤታማና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ የሚረዳ የፌዴራል ድጎማና የጋራ ገቢዎች ቀመር እንዲዘጋጅ በማድረግ፤ የማከፋፈያ ቀመሮቹ በፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና በክልሎች የተመጣጠነ እድገት ላይ ያላቸውን አንድምታ እንዲጠና በማድረግ ሰፊ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱ ተነስቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የዛሬው መድረክ አሁን ያለውን ቀመርና አፈጻጸሙን እንደገና መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከቋሚ ኮሚቴውና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ባለድርሻ አካለት ጋር ግብዓት ለመሰብሰብ የታለመ መድረክ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፊስካል ፌዴራሊዝም ሪፎርም መደረጉንና ይህም በርካታ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን በተገቢው የሕግ አግባብ ለመመለስ ቁርጠኝነት እንደሚፈልግና፤ ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በርብርብና በእኔነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

በቀጣይ ለሚካሄደው የቀመር ማሻሻል ስራ ከሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ጋር ተያይዞ በጥናትና በበቂ መረጃ የተደገፉ ስራዎችን መስራት ለቀመር ማሻሻል ሂደቱ ቁልፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።

በመደረኩ የሚነሱ አስተያየቶችና ሀሳቦች ቋሚ ኮሚቴው ለሚያዘጋጀውና ለምክር ቤት ለሚቀርበው ሀገራዊ ሰነድ ትልቅ ግብዓት ሆኖ እንደሚወሰድም ነው የገለጹት።

ለቀመር ዝግጅት የሚያስፈልጉ መረጃዎች ወቅታዊና ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ የጋራ ስምምነት መደረሱም ተገልጿል።

በመረጃ አቅርቦት ረገድ ኃላፊነት የተጣለባቸው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top