አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ግዙፏ ሁለገብ የጭነት መርከብ በቀጣዩ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የወደብ ማእከል ጅቡቲ መልህቋን እንደምትጥል ተገለፀ

12 Mons Ago
አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ግዙፏ ሁለገብ የጭነት መርከብ በቀጣዩ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የወደብ ማእከል ጅቡቲ መልህቋን እንደምትጥል ተገለፀ

አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ግዙፏ ሁለገብ የጭነት መርከብ በመጪው ሰኔ 17 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የወደብ ማእከል፣ ጅቡቲ መልህቋን እንደምትጥል የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የቀየራት አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ይህች መርከብ ድርጅቱ በ60 አመት ታሪኩ አስተዳድሮ የማያውቀው ግዙፍ መርከብ ነች።

የመርከቧ የመጫን አቅም 65 ሺህ ቶን ሲሆን (በመጫን አቅሟ በዘርፉ አልትራማክስ በሚል መጠሪያ ትታወቃለች) በወቅቱ የሎጅስቲክ ዘርፍ እንቅስቃሴ በጣም አዋጭ ሆና በመገኘቷ ነው በለውጥ የተወሰደችው።

በአንጻሩ ከተገዙ 11 ዓመት የሆናቸው ሁለት የነደጅ ጫኝ መርከቦች ለድርጅቱ አትራፊ ባለመሆናቸው፤ ለመሸጥ አልያም በአዋጭ መርከብ ለመቀየር ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ባለፈው መጋቢት የመርከብ ቅያሬ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ችሏል።

ወደ ስራ ከገባች የ7 ዓመት እድሜ ያላት እና በማርሻል አይላንድስ ተመዝግባ በጀርመን የመርከብ አንቀሳቃሽ ድርጅት ስራ ላይ የነበረችው የአባይ 2 መምጣት ለድርጅቱ የመርከብ ኪራይ እንደሚቀንስለት ተገልጿል።

በመተሳሳይ ድርጅቱ በሌሎች ወደቦች ጭነት በማድረስ በውጭ ምንዛሬ የሚገኘውን ገቢ በይበልጥ እንደሚሳድግለት ነው የተናገረው።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ከኢትዮጵያ ጭነቶች በተጨማሪ የሌሎች አገራትን ጭነት በማጓጓዝ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያገኘ መሆኑም ተጠቅሷል።

አባይ 2 በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከቻይና ሻንሃይ ወደብ ተነስታ ወደ ስራ ከገባችበት ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ የተለያዩ ጭነቶችን ወደ ኮርያ እና ቬትናም ያደረሰች ሲሆን፤ አሁን ላይ ከፍተኛ የብረት ጭነት ይዛ ወደ ሰሜን አውሮፓ፣ ባልቲክ ባህር እያመራች እንደሆነ ተነግሯል።

በተመሳሳይ ድርጅቱ ሌሎች ሁለት 65 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው አልትራማክስ መርከቦችን ለማስገንባት ከቻይና የመርከብ ገንቢ ድርጅት ጋር ድርድር የጨረሰ ሲሆን፤ በቅርቡ ውል እንደሚያስር እንደሚጠበቅ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ግንባታው ከተጀመረ በኋላም ለመረከብ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ የሚገመት ሲሆን፤ የመርከቦቹ መምጣት የድርጅቱን የማጓጓዝ አቅም እና የውጭ ምንዛሬ ገቢውን በይበልጥ እንደሚያሳድግለት ተገልጿል።

ድርጅቱ ከአባይ 2 በተጨማሪ 9 ሁለገብ መርከቦች ያሉት ቢሆንም፤ መርከቦቹ በዘርፉ ሃንዲሳይዝ በመባል የሚታወቁ እና የመጫን አቅማቸው ከ28 ሺህ ቶን ያልበለጠ ነው። ይህም መርከቦቹ በመካከለኛ የርቀት መዳረሻ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top