የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለፀ

1 Yr Ago
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በሲሚንቶ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለፀ
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ ሲሚንቶ ዘርፍ፣ በማዳበሪያ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ኃይሎች ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ በቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀመንበር በሚስተር ሊ ዚያንግ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በቀጣይ ስለሚከናወነው የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ወ/ሮ ሰመሪታ፣ የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን በኢትዮጵያ በኃይል ማመንጫና በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ግንባታዎች ተሳትፎ ሲያደርግ የቆየ ግዙፍ የቻይና ካምፓኒ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ግዙፍ ካምፓኒና ከሌሎችም የቻይና ኢንቨስተሮች ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ሊቀ መንበር ሊ ዚያንግ በበኩላቸው፣ ቡድኑ በኢትዮጵያ የተከዜ ኃይል ማመንጫን፣ የፊንጫ አመርቲ ነሽ ኃይል ማመንጫን፣ ገናሌ ዳዋ 3 ሀይል ማመንጫን እና የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶችን መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡
ቡድኑ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በታዳሽ ኃይሎች ኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የቻይና ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ቡድን ከቻይና ግዙፍ ካምፓኒዎች መካከል የሚጠቀስና በርካታ ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ያለው የኢንቨስትመንት ተቋም ሲሆን ከኃይል ማመንጫ ግንባታዎች በተጨማሪ በመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ተቋም ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top