መንግስት በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

4 Hrs Ago 56
መንግስት በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከ ’አፍሪካ ብሬንስ’ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት በጣም ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ጉባኤ ትርጉም ያለውና የሚተገበር ውይይት እንደሚደረግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በትምህርት ቤት ግንባታና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በድጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

እንደ አፍሪካ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንስራ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።

በትምህርት፣ በቴኖሎጂና በክህሎት ዘርፍ የሚደርገው ይህ ውይይት በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

በጉባዔው ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በጉባኤው የትምህርት፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮችና ልዑካን ቡድን አባላት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር ኢንቨስተሮች እየተሳተፉ ይገኛል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top