ባለፉት ስድስት ወራት የተሰሩት የውጭ ግንኙነት ስራዎች በፈታኝ ሁኔታዎች አመርቂ ስኬቶች የተገኙባቸው እንደሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፣ ባለፉት ስድስት ወራት በውጭ ግንኙነት የተሰሩ ዋና ዋና ስራዎችን እና ወቅታዊ የዲኘሎማሲ እንቅስቃሴዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ነብያት እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማራመድ ተጨባጭ ውጤቶችን ማግኘት ተችሏል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን እና በቀጠናው ሰላም ማስከበር ያላት ሚና እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
ከሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ያስቻሉ ከ128 በላይ የከፍተኛ ባለስልጣናት ጉብኝቶች መደረጋቸው ተገለጿል።እነኚህም ወዳጅነትን ለማጠናከር የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞች እና ወቅታዊ አቋሞች ለማስረፅ ያስቻሉ እንደሆኑ ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ ባለፉት ስድሰት ወራት ከነበሩ ስኬቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ነብያት፤ ይህም በባለብዙ ወገን ዲኘሎማሲ መስክ የኢትዮጵያን ሚና ከፍ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል በተለያዩ ሃገራት በችግር ውስጥ የነበሩ 28 ሺህ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ታቅዶ 33ሺህ ዜጎችን መመለስ መቻሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
ከተለያዩ ሃገራት ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በርካታ ስራዎች መሰራታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለ968 የአጎራባች ሀገራት ተማሪዎች ነፃ የከፍተኛ የትምህርት ዕድል መስጠቷንም አብራርተዋል።