ዳግም ዳኝነት

4 Days Ago 98
ዳግም ዳኝነት

የፍትሐ ብሔር ክርክሮች በሚመሩበት የሥነ ሥርዓት ሕግ በመርህ ደረጃ የመጨረሻ ዳኝነት ሚሰጠው አንዴ ነው። ማለትም ተከራካሪዎችና የሚለያዩበት ነጥብ ተመሳሳይ የሆኑበት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ ላይ በድጋሚ ክስ አቅርቦ ዳኝነት መጠየቅ አይቻልም። ሆኖም የመጨረሻ ፍርድ ያገኘ ጉዳይ ፍርዱን በሰጠው በዚያው ፍርድ ቤት በድጋሚ ሊዳኝ የሚችልበት አግባብም አለ።

በዛሬው የሕጉ ምን ይላል ፅሁፍ በፍትሐ ብሔር ክርክር ላይ ድጋሚ ዳኝነት የማይፈቀድበትን እና የሚፈቀድበትን አግባብ የሚያሳዩ እስከ ፌደራል ሰበር ደርሰው አስገዳጅ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ሁለት ክርክሮች ጋር አያይዘን እናያለን።

1.የአቶ ሱፊያን ይዞታ

አቶ ሱፊያን ቢሾፍቱ ከተማ ቀበሌ 01 ውስጥ ወደ አስር ሺህ ካሬ ሜትር ሚጠጋ ይዞታ ነበራቸው። በዚህ ይዞታቸው ላይ ከአራት ተከሳሾች ጋር ተካሰው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታቸው በመሰረዙ መብት የላቸውም ተብሎ ቢወሰንባቸውም የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቴ ስላልተሰረዘ የቢሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማንጅመንት ኤጀንሲ ሕጋዊ ይዞታዬን ያስረክበኝ ሲሉ ክስ መሰረቱ።

የአድአ ወረዳ ፍርድ ቤትም የከተማ መስተዳድሩ መሬቱን ለአቶ ሱፊያን እንዲያስረክብ ወሰነበት። ይህ ውሳኔ በሌለንበት ስለተሰጠ መብታችንን ነክቷል ያሉት አቶ ክፍሉና ወይዘሮ ዘውዴ ይዞታዉ የአቶ ሱፊያን ሳይሆን የኛ ነው፤ ከእጃችን ወጥቶም አያውቅም በማለት ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቶታ አቀረቡ። በይዞታው ባለመብትነት ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ስለሰጠና አቶ ሱፊያን በመከነ ካርታ መክሰስ ስለማይችሉ የተሰጠውን ውሳኔ እንቃወመዋለን ይሻርልን ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ።

አቶ ሱፊያን ይዞታውን ከ1983 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ግብር እየከፈልኩ ስጠቀምበት ነበር። አቶ ክፍሉና ወይዘሮ ዘውዴ የመሬት ይዞታዬን ማረስ የጀመሩት በሕገ ወጥ መንገድ በመያዝ ነው፤ ሲሉ መልስ ሰጡ። የቢሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ ደግሞ የአቶ ሱፊያን ካርታ ስለተሰረዘ በይዞታው ላይ መብት የላቸውም ሲል መልስ ሰጠ።

የአድአ ወረዳ ፍርድ ቤትም መቃወሚያውን መርምሮ ውሳኔውን የሚያስለውጥ ሆኖ ስላላገኘው መቃወሚያውን ውድቅ አድርጎ ውሳኔውን አፀናው።

እነ አቶ ክፍሉ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል በሚል ለኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ። የኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት የሰበር ሰሚ ችሎትም አቶ ሱፊያን መብት የላቸውም ብሎ ውሳኔ ሰጥቶ እያለ የስር ፍርድ ቤቶች ድጋሚ ክስ በቀረበበት በዚያው ጉዳይ ላይ ግራ ቀኙን አከራክረው ውሳኔ በመስጠታቸው የሕግ ስህተት ፈፅመዋል በማለት የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሻረው።

አቶ ሱፊያን በተራቸው ካርታዬ ተሰርዟል በሚል የተሰጠው ውሳኔና መሬት ልማት ኤጀንሲው ይዞታዬን እንዲያስረክበኝ የተሰጠው ፍርድ የተለያየ ጭብጥና ተከራካሪ ያላቸው በመሆናቸው ድጋሚ የቀረበ ክስ በሌለበት የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት ስለፈፀመ ውሳኔው ይሻርልኝ ሲሉ ለፌደራል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

ለመሆኑ የአቶ ሱፊያን ውሳኔ በተሰጠበት ጉዳይ ድጋሚ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው? ሰበር ምን ሚወስን ይመስላችኋል? በዚህ ጉዳይ ላይ ያላችሁን የሕግ ግንዛቤ ለመፈተሽ የሰበርን ውሳኔ ከማንበባችሁ በፊት ውሳኔውን ገምቱ ግምታችሁንም በአስተያየት መስጫው አጋሩን።

በአቶ ሱፊያን ጉዳይ ሰበር ምን አለ?

አቶ ሱፊያን ከዚህ ቀደም እነ አቶ ክፍሉና ሌሎች ሦስት ሰዎች ላይ ክስ አቅርበው ይገባኛል የሚሉት የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ምስክር ወረቀት በመሰረዙ መብት የላቸውም በሚል ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5(1) መሰረት ተከራካሪዎቹን በመቀየርና የቢሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲን ተከሳሽ በማድረጋቸው ብቻ ጭብጡ እንደተቀየረ አድርገው ድጋሚ አዲስ ክስ ማቅረብ አይችሉም በማለት የኦሮሚያ ክልል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትን ውሳኔ አፅንቶታል። ውሳኔውን የሰጠው ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በሰ.መ.ቁ 130410 ሲሆን በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 22 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

 

2.ዳግም ዳኝነት እና ሀሰተኛ ማስረጃ

አቶ ግርማና ወይዘሮ አልማዝ የጋራ መፀዳጃ ቤት እየተጠቀሙ በሠላም ሚኖሩ ጎረቤታሞች ነበሩ። ከሳሽ አቶ ግርማ መፀዳጃ ቤቱን በጋራ መጠቀም ባለመቻሌ የራሴን መፀዳጃ ቤት ለመገንባት የእድሳት ፍቃድ አውጥቼ ቤቱን በማፍረስ ላይ እያለሁ ሥራውን እንዳቆም በመደረጌ ሁከት ስለተፈፀምመብኝ ሁከቱ ይወገድና የመፀዳጃ ቤት ሥራውን እንዳጠናቅቅ ይወሰንልኝ ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ ላይ   በፌ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት ክስ አቀረቡ።

ወይዘሮ አልማዝም መፀዳጃ ቤቱን ራሳቸው ስለሰሩትና በይዞታቸው ስር ስለሚገኝ ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ለክሱ መልስ ሰጡ።

ፍርድ ቤቱ የሚገኝበትን ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝን መፀዳጃ ቤቱ በማን ይዞታ ስር እንደሆነ አጣርቶ መልስ እንዲሰጥ አዘዘ። ወረዳውም መፀዳጃ ቤቱ በወይዘሮ አልማዝ ይዞታ ስር እንደሚገኝ በፅሁፍ አረጋገጠ። ፍርድ ቤቱም ወይዘሮ አልማዝ ይዞታቸው ላይ ስለሚገኝ የመፀዳጃ ቤቱ ባለቤት ናቸውና መፍቀድም መከልከልም ስለሚችሉ ክሱን አልተቀበልኩትም ሲል አቶ ግርማ ላይ ወሰነባቸው።

አቶ ግርማም ለወረዳው የሰጠው ምላሽ የቤታቸው የቤ.ቁ 417 የጋራ መገልገያ የሆነውን የመፀዳጃ ቤት በቤ.ቁ 418 ስር ያጠቃለለ በመሆኑ ወረዳው ለፍርድ ቤቱ የፃፈው ደብዳቤ ሊሻር ይገባል ሲሉ አመለከቱ። ወረዳው ቀደም ብሎ የፄፈው ደብዳቤ ሀሰተኛ መሆኑን በሌላ ደብዳቤ አረጋገጠላቸው። ለፍርድ ቤቱም ውሳኔ የሰጠው ሀሰተኛ መረጃን መሰረት በማድረግ በመሆኑ ወረዳው ቀደም ብሎ የሰጠውን ማስረጃ በመጥቀስ የፃፈውን ደብዳቤ በማስረጃነት አያይዘው ውሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት በድጋሚ ዳኝነት እንዲታይላቸው አቤቱታ አቀረቡ። ፍርድ ቤቱ ግን ውሳኔው በድጋሚ እንዲታይ ያቀረቡት ማስረጃ በሀሰተኛና በወንጀል ነክ ተግባሮች በተገኙ የሰነድ ማስረጃዎች  መሰጠቱን ስለማያሳይ ፍርዱ በድጋሚ ሚታይበት ምክንያት የለም በሚል አቤቱታቸውን ውድቅ አደረገው። ይህ ውሳኔ በባህሪው ይግባኝ የማይባልበት ነው።

አቶ ግርማ ለፌ/ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የስር ፍርድ ቤት ፍርዱን በድጋሚ አላይም በሚል የሰጠው  ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት በመሆኑ ይታረምና ብይኑ ይሻርልኝ ሲሉ የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።

ሰበር ሰሚ ችሎቱም የግራ ቀኙን የሰበር ክርክርና የስር ፍርድ ቤት መዝገብን መርምሮ ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰ.መ.ቁ 91968 የሰጠው ውሳኔ  በሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 15 ላይ ታትሞ ወጥቷል።

ሰበር በዚህ ጉዳይ ላይስ አንድን የፍትሐ ብሔር ክስ በዳግም ዳኝነት ስለማየት የሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ምን ይመስላችኋል? ውሳኔውን ከማንበባችሁ በፊት ገምቱና በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ግምታችሁን አጋሩን።

ሰበር በነ አቶ ግርማ ጉዳይ

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 6(1) መሰረት በሀሰተኛ ማስረጃ፣ ምስክር፣ መደለያ ወይም በወንጀል ነክ ተግባር ላይ በተመሰረተ ማስረጃ ውሳኔ ከተሰጠ፣ ውሳኔው መብቱን የሚጎዳው ሰው አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ውሳኔው ከመሰጠቱ በፊት የሀሰት ማስረጃውን ማወቅ ካልቻለና ይህ የሀሰት ተግባር ቢገለጥ ኖሮ ውሳኔውን ሊያስለውጥ የሚችል ከሆነ ማስረጃው ሀሰት መሆኑን የሚያሳይ አዲስ ማስረጃ ካገኘበት ቀን ጀምሮ ከአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ፍርድ ቤቱም ተከራካሪው ወገን በአቤቱታው ላይ ሚሰጠውን መልስና ክርክራቸውን መርምሮ ዳኝነቱ ድጋሚ ሊታይ ይገባል ወይም አይገባም ሚለው ነጥብ ላይ ይግባኝ የሌለበት ውሳኔ ይሰጣል።

የነ አቶ ግርማ ጉዳይን ከላይ ካነሳነው የሕግ ድንጋጌ አንፃር የመረመረው የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ከላይ የጠቀስነው የሕግ ድንጋጌ ዓላማ የመንግስት ባለስልጣናት የተሳሳተ መረጃ በመስጠታቸው ወይም አቶ ግርማ ደብዳቤውን የፃፈው የወረዳው ኃላፊ የጋራ የሆነውን መፀዳጃ ቤት የወይዘሮ አልማዝ የግል እንደሆነ አድርጎ የሀሰት ማስረጃ መስጠቱን ወረዳው ድጋሚ በፃፈላቸው ደብዳቤ እስካረጋገጡ ድረስ የሚመለከተው የወረዳው ኃላፊ ይህን የሀሰት ማስረጃ የሰጠበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ሊጠየቁ ስለማይገባ ዳግም ዳኝነት ሊታይ አይገባም ሲል ፍርድቤቱ በሰጠው ብይን የሕግ ስህተት ፈፅሟል። በመሆኑም የስር ፍርድቤቱ ጉዳዩን በድጋሚ ዳኝነት ዓይቶ እንዲወስን ለስር ፍርድ ቤት መልሶለታል።

 

የሕግ ባለሙያ ኪዳኔ መካሻ  


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top