ኢትዮጵያን ሲወዱ ያለ ሐይማኖት፣ ብሔር እና ባህል ልዩነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያንን ታላቅነት የሚመሰክሩት በተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሌሎች ለኛ የሚሰጡትን ቦታ ለታላላቆቻችን እንደማንሰጥ እና ሐብታችንን እያባከንን እንደሆነ በቁጭት ይናገራሉ፡፡
አየሯን ጨምሮ የኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሐብት ከሕዝቧ ተርፎ ለሌሎች የሚበቃ እንደሆነ እና ኢትዮጵያውያን ግን ይህን ሀብታቸውን አለማወቃቸው ያስቆጫቸዋል፡፡
ላለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ እና የዓረቦች ግንኙነት፣ የእስልምና ታሪክ፣ የነጃሺ እና የቢላል ታሪክ እንዲሁም የመካከለኛ ምሥራቅ ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ኮከብ እንደነበረች እና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በነበሩት ግብፃዊ ቡቱሩስ ቡቱሩስ ጋሊ ተንኮል ወደቧን እንድታጣ ሚና እንደነበራቸው ይገልጻሉ፡፡
በኢትዮጵያ የሚመደቡ አብዛኛዎቹ የግብፅ ድፕሎማቶች የግብፅ ደህንነቶች እንደሆኑ እና ዓረብኛ ቋንቋ አለመቻላችን ለነሱ ሰለባ እንዳደረገን ይናገራሉ፡፡
ፕሮፌሰር አደም ካሚል የተወለዱት በሰሜን ወሎ የጁ ገፍራ በሚባል አካባቢ 1947 ዓ.ም ነው፡፡ በሰባት ዓመታቸው የቤተሰቦቻቸው ቤት መቃጠል እና የቤተሰቦቻቸው ህልፈት ለስደት ዳረጋቸው፡፡ ታላቅ ወንድማቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ዜግነት ስለነበራቸውም ወስደው እዚያው አስተማሩአቸው፡፡
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በመካ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ንጉሥ አብዱላዚዝ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሕዝብ አስተዳደር እና ፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ በወቅቱ በዚያ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በዲግሪ የተመረቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም በወቅቱ በነበረው ሥርዓት ተቀባይነት ሳያገኙ እንዲሁም የትምህርት ማስረጃቸውም ዕውቅና ሲያጣ ተመልሰው ወደ ስደት ሄዱ፡፡ ወደ ፓኪስታኗ አልበዲን ዩኒቨርሲቲ በማቅናት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡
ወደ ሳዑዲ በመመለስም "የአፍሪካ ቀንድ" የሚል መጽሔት ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ዓላማቸውም ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዓረቡ ዓለም ያላትን ቦታ እንድታገኝ ማስቻል ነበረ፡፡ ኢትዮጵያ በረሃብ እና ችግር ብቻ መታወቋ ያስቆጫቸው ስለነበረም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት መጽሔቱን ተጠቅመዋል፡፡ የመጽሔቱ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ያላማራቸው ባለሥልጣናትም ወደ እስር ቤት አስገቡአቸው፡፡ ለሦስት ዓመታት በወህኒ ቤት ከቆዩ በኋላም እንደገና ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ በጥናት እና ምርምር ዘርፍ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በመካከለኛ ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ከ33 በላይ የምርምር ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከስድስተ መቶ በላይ ቃለ መጠይቆችን አድርገዋል፤ በሞሮኮ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች፣ በኩዌት፣ በአሜሪካ እና በካናዳ ለሚገኙ ስምንት ድርጅቶች ሴሚናሮችን ይሰጣሉ፡፡ የሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ የአፍሪካ ሊቃውንት ጉባኤ መሥራች እና አባል ናቸው፡፡
ከልጅነት ዕደሜአቸው ጀምረው ከኢትዮጵያ የወጡ በመሆናቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ዜግነት የማግኘት ዕድል እንደነበራቸው የሚገልጹት ፕሮፌሰር አደም፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከልባቸው ስለሚወድዱ ዜግነታቸውን እንዳልቀየሩ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምክንያት ያገኙት ክብርም በጣም ትልቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ቤትም እያሉ የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያውቁ መምህራኖቻቸው ይረዱአቸው ነበር፡፡
መምህራኖቻቸው "ነቢዩ መሐመድ ኢትዮጵያ የእውነት እና የፍትህ ምድር ናት፣ እንዳትነኳት" ብለው የተናዘዙላት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ገልጸው ያከብሩአቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ዓለም እውነት እና ሀቅ ባጣችበት በዚያ ወቅት የነቢዩ መልዕክተኞችን እና መልዕክቱን የተቀበለችው ኢትዮጵያ እንደሆነች እና ይህም በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው እንዳሉአቸውም ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአድዋ በወራሪዎች ላይ የተጎናጸፈችው ድል ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርነት መሆኑ የፈጣሪ ፈቃድም እንደፈጸመች ማሳያ እንደሆነም ከመምህራኖቻቸው መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለሰው ልጆች ፍትህ የታገለች እና ዋጋ የከፈለች ድልም የተጎናጸፈች መሆኗን በዓለም ፊት አንገቷን ቀና እንደሚያደርግ እና ዜጎቿንም እንደሚያኮራ ይናገራሉ፡፡
የመጀመሪያው እስላማዊ ስደት የተካሄደው ወደ ኢትዮጵያ መሆኑን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር አደም፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡትን የአይሁድን፣ የክርስትናን እና የእስልምና እምነቶችን አስተባብራ በሕብር ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ብቻ ነች ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የግብፅ ህይወት የሆነው የዓባይ ምንጭ መሆኗን በማውሳትም፣ አባይ ባይኖር ኖሮ ሱዳንም ሆነች ግብፅ ባልነበሩ ይላሉ፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ የግብፅ መጋቢ እና ባለውለታ ነች በማለት የኢትዮጵያን አስተዋጽኦ ያብራራሉ፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ዜጎችን ተቀብሎ መንከባከብ፣ የአየር ንብረቷ፣ የዓረብ እና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አንድ ቤተሰብ መሆን ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ቦታ ከፍ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አሳሳቢ እየሆነበት ባለው መካከለኛ ምሥራቅ ውስጥ ኢትዮጵያ የያዘችው አመቺ የአየር ንብረት፣ ለም አፈር፣ የውሃ ሀብት እና ሌሎች እምቅ ሀብቶች ከተጠቀምንባቸው መልካም ዕድሎች እንደሆኑም ይገልጻሉ፡፡
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብፅ የያዘችው አቋም አሁን እውነት የውሃ እጥረት ስለሚገጥማት ሳይሆን በቀጣይነት ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ካለማች የመካከለኛው ምሥራቅን ታላላቅ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ተፅዕኖዬን ትቀንስብኛለች ብላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በዚህም ምክንያት ግብፅ የኢትዮጵያ መረጋጋት እና ኃያልነት አትፈልግም በማለት የግብፅን አቋም ያሳያሉ፡፡ ግብፆች ኢትዮጵያን እና አባይን በተመለከተ ብቻ 560 ኮንፈረንሶችን፣ 1 ሺህ 560 ጥናቶችን እና 222 መጽሐፍቶችን በዓረብኛ እንዳዘጋጁ ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዓረብኛ ቋንቋ ትኩረት ስላልተሰጠው ግብፆች በዓረብኛ ስለኢትዮጵያ የሚያቦኩትን እና የሚጋግሩትን አናውቅም ይላሉ በቁጭት፡፡
በታሪክም በተፈጥሮ ሀብትም የምትበልጠው ኢትዮጵያ በውስጧ በሚፈጠሩት ልዩነቶች ምክንያት እጇን ለልመና መዘርጋቷ ሲያስቆጫቸው ኖሯል፡፡ ይህንን ታሪክ መፋቅ እና ወደ ኃያልነታችን መመለስ አለብን በማለት ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸውም ሀገራቸውንም አያውቁም ይላሉ፡፡ ወደ ስደት የሚሄዱት ሀገራቸውን እንዲያውቁ ስላልተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፣ መንግሥታት ከሕዝቡ ጋር መናባብ አለባቸው ይላሉ፡፡ እናም ከእንቅልፋችን ነቅተን ወደ ታላቅነታችን መመለስ እንዳለብን ይመክራሉ፡፡
ዛሬ ስለ ዓባይ እየተሟገቱ ያሉ እነ መሐመድ አል አሩሲ እና ኡዝታዝ በሽር ጀማልን ያስተማሩት ፕሮፌሰር አደም፣ ግብፆች በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በያዙአቸው ቦታዎች ኢትዮጵያ ውኃዋን እንዳትጠቀም ጫና ሲያደርጉ ኖረዋል ይላሉ፡፡
በለሚ ታደሰ