በስልጤ ዞን ሰሞኑን በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የተፈናቃይ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዞኑ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ጽ/ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፅ/ቤቱ ኃላፊ ወሲላ አሰፋ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለፁት፤ በጎርፉ አደጋው 7ሺ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ 1300 ሄክታር መሬት ማሳ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፤ 6 ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 1ሺ ቤቶች በጎርፍ ተውጠዋል፡፡
በማእላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በስልጢ እና ምስራቅ ስልጢ ወረዳዎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ እየተፈናቀሉ ያሉ ሰዎች ቁጥር አሁንም እየጨመረ መሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ወረዳዎቹ በጎርፍ ተውጠው የነበሩ ቀበሌዎች ከ6 ወደ 8 ማደጉንና በውሃ የተዋጡ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 6 መድረሱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትሮሎጂ ትንበያ መረጃ የዝናቡ መጠን ቀጣይነት እንደሚኖረው ያመለክታል ያሉት ኃላፊዋ፤ ዝናቡ እስከቀጠለ ድረስ አሁንም የጎርፍ ውሃው መጠን እንደሚጨምርና ጎርፉ ያረፈበት ስፍራ መጠን እየሰፋ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በዓመት ሶስት ጊዜ ማምርት የሚችል አምራች አከባቢ ቢሆንም በጎርፍ አደጋው ምክንያት በ1300 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ቋሚ ተክልና ማሳ ላይ የሚገኝ ሰብል ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኗል ብለዋል ወ/ሮ ወሲላ፡፡
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና የስልጤ ዞን እያንዳንዳቸው 300 ኩንታል ዱቄትና ምግብ ነክ ሰብዓዊ እርዳታ በአደጋው ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የገለፁት፡፡
የተለያዩ ወረዳዎች፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ባለሀብቶች እና የበጎ አድራጎት ማህበራት ለተጎጂ የህብረተሰብ ክፍል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አንስተው፤ የተፋናቃይ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመሆኑ ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና ከክልሉ ጋር በጋራ በመሆን መንገዱ አመቺ በሆናበት በምስራቅ ስልጢ ወረዳ የስካቫተር ማሽን ተከራይቶ በማስገባት ለጎርፍ ውሃው መሄጃ መንገድ ለመስራት ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ነው ኃላፊዋ የተናገሩት፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን የክልልና የፌደራል መንግስት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የዞኑ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ወሲላ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
በላሉ ኢታላ