የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚጋፉ ኃይሎችን ማስተናገድ ማቆም አለበት፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

4 Mons Ago 470
የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚጋፉ ኃይሎችን ማስተናገድ ማቆም አለበት፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚጋፉ ኃይሎችን ማስተናገድ ማቆም እንዳለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በወቅታዊ አካባቢያዊ ጉዳይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራትም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሠመረ ግንኙነት እንዲኖራት ጥረት ከማድረግ ወደኋላ እንደማትል ሚነስትሩ አንስተዋል።

በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በዴፕሎማሲያዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።

ይሁንና አንዳንድ የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት ልዩነትን ማስፋት የአዘቦት ተግባራቸው አድርገውታል ብለዋል።

ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቆም ኢትዮጵያ ያደረገችው መስዕዋትነት ተዘንግቶ ከመንግስት በማይጠበቅ መልኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ማንቋሸሽ ላይ ተጠምደዋል ብለዋል።

ሶማሊያ ወደ ውይይት እንድትመጣና አልሻባብ ላይ የሚደረገው የፀረ ሽብር ትግል አጠናክሮ መቀጠል የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑንም አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ተናግረዋል።

አልሻባብ ከሶማሊያ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ስጋት በመሆኑ የጋራ የፀረ ሽብር መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

ሶማሊያ የአካባቢውን ሰላም ከማይፈልጉ አካላት ጋር የምታደርገው እንቅስቃሴ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም ብለዋል።

በዚህም የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉ ኃይሎችን ማስተናገድ ማቆም እንዳለባትም አምባሳደር ታዬ ገልፀዋል።

በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል የኢትዮጵያ የደህንነት አደጋ ምንጭ መሆን የለበትም ብለዋል።

የብዙ ሀገር ፍላጎትም በሰላም ማስከበር ኃይል ላይ ኢትዮጵያ ከሌለች የመጣው በጎ ነገር ሁሉ ሊቀለበስ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያሉ አለመግባባቶች በሰላማዊ አማራጭ እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በሙሉ ግርማይ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top