አዲስ አበባ በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ ተሰየመላት

4 Mons Ago 553
አዲስ አበባ በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ ተሰየመላት

በጀርመን የላይፕዚግ ከተማ በአዲስ አበባ ስም የተሰየመ አደባባይ በላይፕዚግ እና በአዲስ አበባ መካከል የእህትማማች ከተማ አጋርነት 20ኛ ዓመት የማክበር ስነ-ስርዓት ላይ ተመርቆ ተከፈተ።

በታሪካዊው የላይፕዚግ እምብርት ላይ የተካሄደው ስነ-ስርዓት ላይ የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካዮች፣ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮች፣ የላይፕዚግ ባለስልጣናት እና በአካባቢው ያሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

አደባባዩ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግ በአፅንኦት ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ወክለው የተገኙት የከንቲባ አማካሪ አቶ አሻግሬ ገብረወልድ፤ የአደባባዩ መመረቅ ለሁለቱ ከተሞች እና ለሁለቱ ሀገራት ዘለቄታዊው ግንኙነት የላቀ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአደባባዩ በአዲስ አበባ ከተማ መሰየም አጋርነትንና የጋራ ታሪክን ከመዘከር ባለፈ በቀጣይ ለሚደረጉ የሁለትዮሽ ትብብሮች መንገድ የሚከፍት መሆኑን መግለፃቸውን የከንቲባ ፅ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

ዝግጅቱ ሁለቱ ከተሞች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የጋራ ዕድገትን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ ሲሆን፣ አዲስ አበባም ይህን ጠቃሚ አጋርነት ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ተወካዩ ጠቅሰዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top