በሚቀጥሉት 10 ቀናት ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ይኖራል፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

4 Mons Ago 719
በሚቀጥሉት 10 ቀናት ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ይኖራል፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
በሚቀጥሉት 10 ቀናት ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
 
የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ እና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምርመራ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ባደረጉት ቆይታ፤በተያዘው የክረምት ወቅት እስከ መስከረም ወር የሚኖረው የዝናብ መጠን እና ስርጭት ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።
 
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ ቦታዎች መካከል የአዋሽ፣የኦሞ፣ ግቤ፣የዓባይ እንዲሁም የተከዜ ተፋሰሶችን ለአብነት የጠቀሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፤ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
በቆቃ ፣ተንዳሆ ፣ተሰም በመሳሰሉ ግድቦች ላይ የውኃ ሙላት ሊያጋጥም ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ም/ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
 
በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ በጋንቤላ፣ በአብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ፣በሶማሌ ክልል ሰሜናዊ ክፍል አብዛኛው ቦታዎች ከዓመታዊው የዝናብ መጠን 80 በመቶ የሚሆነው ስርጭት የሚደርሳቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
 
ባለፉት ሁለት ወራት የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደነበራቸውም አመላክተዋል።
 
በሀገሪቱ 170 በሚሆኑ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር እስከ 118 ሚሊ ሜትር እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደተመዘገበ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
 
ከአትላቲክ እና ከደቡባዊ ህንድ ውቂያኖስ በመነሳት ወደ ሀገሪቱ የሚገባው እርጥበት አዘል አየር፣ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊጠናከር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብለዋል።
 
በተጨማሪም በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚፈጠረው ጠንካራ የደመና ክምችቶች ላይ በመነሳት በተለይ በምስራቅ አማራ ፣በደቡብ አፋር ፣በምስራቅ ሸዋ እንዲሁም በመካከለኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር እስከ 100 ሚሊ ሜትር እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ጠቅሰዋል።
 
የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው የዝናብ ስርጭት የግብርና ስራዎችን ለማከናወን ጠቀሜታ እንዳለው በመግለጽ፤ሆኖም ግን የሚኖረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን አሉታዊ ችግሮች ሊፈጥር ስለሚችል በተለይም በማሳዎች አካባቢ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
በከተሞች አካባቢ ያለውን ስጋት ለመቀነስ የውኃ ማፋሰሻ ትቦዎቸን በአግባቡ ማጽዳት እና ጎርፍን መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ም/ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top