በወንጀለኞች ላይ የሚሰጡ ቅጣቶች የሕጉን ክፍተት ያሳያል፦ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ

4 Mons Ago 655
በወንጀለኞች ላይ የሚሰጡ ቅጣቶች የሕጉን ክፍተት ያሳያል፦ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ
በወንጀለኞች ላይ የሚሰጡ ቅጣቶች የሕጉን ክፍተት እንደሚያሳይ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ወ/ሮ አዲስ መሀመድ ገለጹ፡፡
 
በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ አስገድዶ መድፈር እና ጥቃቶች እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያው አደባባይ እየወጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
 
ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ወ/ሮ አዲስ መሀመድ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በወንጀለኞች ላይ የሚሰጡ ቅጣቶች የሕጉን ክፍተት ያሳዩ ሲሆን፣ በቅርቡ የሰማነው በህጻን ሄቨን ላይ የደረሰው ወንጀል የመደፈር ብቻ ሳይሆን 3 እና 4 ወንጀሎች ናቸው ብለዋል፡፡
 
ከ13 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት እንዲሁም በላይ በማለት ሕጉ የወንጀሉን ቅጣት ይከፋፍለዋል ያሉት ጠበቃዋ፤ የ7 ዓመቷ ህጻን ሄቨን ላይ የደረሰው አስነዋሪ ወንጀል፣ ህጻኗ ምን እንደተከናወነ እና ስለ አስገድዶ መደፈር ምንነት መለየት ሚያስችላት እድሜ ላይ እንኳን አለመሆኗል ገልጸዋል፡፡
 
ሕጉ ውስጥ እንደዚህ ያለ ዘግናኝ ወንጀል ሲፈጸም የሞት ቅጣት የለውም ያሉት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪዋ፤ ነገር ግን ቀጥሎ ምን አስከተለ የሚል አግባብ ስለመኖሩ አንስተዋል። ሆኖም ግን የራሱ የሆነ የሕግ ክፍተቶች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል፡፡
 
እንዲህ ያለ ክፍተትን ሁሉም የፍትሕ ተቋማት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የሚስተካከል ነው የሚሉት ጠበቃዋ፤ እነዚህ የፍትሕ አካላት ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ እና ፍርድ ቤት ናቸው ብለዋል፡፡
 
ክስ ሲመሰርትም ከአስገድዶ መድፈሩ በዘለለ ለተደራራቢ ወንጀሎች ሌሎች የቅጣት አንቀፆች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ በዚህ መልኩ ክስ መመስረት እንደሚገባ አንስተዋል።
 
ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ወ/ሮ አዲስ፤ ወንጀሎቹ ተደራራቢ ሲሆኑ ለቅጣቶች ማክበጃ ምክንያት ስለሚሆኑ፣ የወንጀሉን አፈጻጸም ዝርዝር ማስረጃ በመያዝ ክስ መመስረት እና አስተማሪ ሊሆን የሚችል ቅጣት እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top