በሐረሪ ክልል የሚገኘውን አነስተኛ የእርሻ መሬት በአግባቡ ተጠቅሞ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን አነስተኛ መሬት በአግባቡ ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ በ2016/17 የመኸር እርሻ 8 ሺህ 853 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች እየለማ መሆኑን በማከል።
በክልሉ ሦስት የገጠር ወረዳዎች በሚገኙ ማሳዎች ላይ እየለሙ የሚገኙት ሰብሎችም ማሽላ፣ በቆሎ እና ስንዴ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም ዘንድሮ ከሃረማያ ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ የተገኘውን 100 ኩንታል "መልካም" የተሰኘ የማሽላ ዝርያ በኢንሼቲቭ መልክ መዘራቱንና ሰብሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በ800 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው ይኸው የማሽላ ሰብልም የዝናብ እጥረትን በመቋቋም በአጭር ጊዜ ምርት መስጠት የሚችል የተሻለ የማሽላ ዝርያ መሆኑን ተናግረዋል።
ለመኸር ምርታማነት ማደግ አስፈላጊው የግብርና ግብዓት ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ያመለከቱት አቶ ነስረዲን፤ በምርት ዘመኑ እየለሙ ካሉ ሰብሎች 210 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰበሰብ መታቀዱንም አስረድተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማና ገጠር ወረዳዎች የተጀመረው የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት መርሃግብር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይም በወተት፣ እንቁላል፣ በማር ምርት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ስራዎች በክልሉ የግብርና ምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከማስቻሉ በተጨማሪ አምራቹንና ተጠቃሚውን እርስ በርስ በማገናኘት ምርቱ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ እያስቻለ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን ከለማው 8 ሺህ 533 ሄክታር መሬት ከ168ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል።