ደብረ ታቦር ወይም ቡሄ ሐይማኖታዊ እና ባሕላዊ አንድምታው

4 Mons Ago 670
ደብረ ታቦር ወይም ቡሄ ሐይማኖታዊ እና ባሕላዊ አንድምታው
ነሐሴ 13 ቀን በሐይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ስያሜው ቦታው ላይ ተመስርቶ ደብረ ታቦር ይባላል፡፡
 
"ደብር" ተራራ "ታቦር" ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠበት ቦታ ሲሆን፣ ቃላቱ ተጣምረው "ደብር-ታቦር" ወይም "የታቦር ተራራ" የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
 
ይህ በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ደብረ ታቦር የሚባል ሲሆን "ቡሄ" በመባልም ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት "መላጣ፣ ገላጣ" ማለት ነው፡፡
 
በሀገራችን ካሉት አራቱ ወቅቶች መካከል ክረምት ጭጋጋማ እና ደመናማ ነው፡፡ ይህ የክረምቱ፣ ጭጋግ እና ደመና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ መታየት የሚጀምረው ከደብረ ታቦር በኋላ ስለሆነ ነው መላጣ፣ ገላጣ መባሉ፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ነው "ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት" የሚባለው፡፡
 
በሌላ በኩል ደብረ ታቦር ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበት እና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበ ዕለት ስለሆነ "የብርሃን" ወይም "የቡሄ" እንደሚባል የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡
 
ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ብራ የሚያመራበት እና ወገግታ የሚታይበት፤ ደመናው ተገፍፎ ሰማዩ ጥርት እያለ የሚሄድ ስለሆነ ከቡሄ በኋላ ክረምቱ እየቀለለ ይሄዳል፡፡ ዕለቱ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ህጻናት እና እረኞች በደስታ የሚውሉበት ዕለት ነው፡፡
 
ልጆች ሙልሙል ዳቦ ተጋግሮ እስኪጠግቡ በወተት የሚበሉበት፤ እረኞች ከሆኑ ከከብቶች ጥበቃ ነጻ የሚሆኑበት፣ በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ ሙልሙላቸውን ይዘው ከብቶቻቸውን የሚሰማሩበት ነው፡፡
 
ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በገለጠ ጊዜ አካባቢው ብርሃን ስለሆነ እረኞቹ ሌሊት መሆኑን ባለማወቃቸው ወደ ቤት ሳይመለሱ ስለቀሩ ወላጆቻቸው ስንቅ ይዘውላቸው መሄዳቸውን ለማመላከት እንደሆነ ይነገራል፡፡
እረኞቹ ጅራፍ ሠርተውም ያጮሃሉ፤ ይህም ድምጸ መለኮት የተሰማበት ምሳሌ መሆኑን አባቶች ያመሰጥራሉ፡፡
 
በበዓሉ ዋዜማ ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ "ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …" እያሉ ይጫወታሉ፡፡ እናቶችም ካዘጋጁት ሙልሙል ዳቦ ይሰጧቸዋል፡፡ የቡሄ ጨዋታ አሁን አሁን ጊዜው ተለውጦ ሳንቲም መሰብሰቢያ ቢሆንም፣ በቀድሞ ጊዜ ሕፃናቱ "ቡሄ" እያሉ የሚሉትም ዳቦውን ነው፡፡
 
የቡሄ ዕለት ማታ በየቤቱ እና በየአብያተክርስቲያናቱ ችቦ ይበራል፤ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ችቦ መብራቱም ወላጆች ለልጆቻቸው ስንቅ ይዘው ሲሄዱ ችቦ አብርተው እንደሄዱ ማሳያ እንደሆነም ይነገራል፡፡
 
ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ሁሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡
 
የአብነት ትምህርት ቤቶች (የቆሎ ትምህርት ቤቶች) ባሉባቸው አካባቢዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ሐዋሪያቱን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብን እና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመሆን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) በልዩ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡ የአብነት ተማሪዎቹ "ስለ ደብረ ታቦር" እያሉ እህል እየለመኑ ጠላ ጠምቀው፣ ዳቦ ጋግረው፣ ቆሎ ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ምእመናንን ያበላሉ ያጠጣሉ፡፡
 
አሁን አሁን በተለይ በከተማ ዙሪያ የቡሄ በዓል ባሕላዊ ትውፊቱን እየለቀቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙ እና ዜማው የልመና እና ሳንቲም መሰብሰቢያ መሆኑ በጣም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡
 
በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያውቁ ልጆችም እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህ ከባሕልም ከሐይማኖትም አንጻር መታረቅ እንዳለበትም የብዙዎች አስተያየት ነው፡፡
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top