ፍትሕን የምትሻዋ ነፍስ

2 Mons Ago 742
ፍትሕን የምትሻዋ ነፍስ

በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ብዙ ህፃናትና ወጣቶች ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸው በማህበራዊ ትስስር ገፅ መነጋገሪያ ሲሆኑ ህዝቡም ስለነሱ ፍትህ ሲጠይቅ ተመልክተናል።

ልጆች ትምህርት ቤት በሂዱበት ጠፍተዋል፣ ወጣቶች በገዛ የትዳር አጋራቸው የአሲድ ጥቃት ሰለባ ሁነዋል፣ ታዳጊዎች በሚማሩባቸው ቦታዎች አብረዋቸው በሚማሩ ወንድ ተማሪዎች ፆታዊ ጥቃት አስተናግደዋል።

ጥቃት ፈፃሚዎችም በህግ አግባብ ቅጣት ሲያገኙ አስተውለናል።

በቅርቡ በባህርዳር ከተማ ከሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ በአንድ ግለሰብ ምክንያት ህይወቷ ያለፈው የሰባት አመቷ ታዳጊ ሄቨን ጉዳይም የብዙዎችን ልብ የሰበር አሳዛኝ ክስተት ነው።

ጉዳዩ ብዙዎችን አሳዝኗል፣ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት አነጋግሯል፣ እናቶች በጭንቀት ፍትህ እያሉ እንዲጠይቁ አድርጓል።

ወንጀሉ የተፈፀመው ሐምሌ 25 ቀን 2015 ሲሆን፤ የምዕራብ ጎጃም ዞን አቃቤ ህግ በቁጥር 063128 በቀን 19/01/2016 በወንጀል ቁጥር 620/3 በመጥቀስ ክስ አቅርቦበታል።

ውሳኔውም ጌትነት ባይህ የተባለው ግለሰብ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ከጥዋቱ 3 ሰዓት በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 14 ውስጥ ህፃን ሄቨን አወት የተባለችውን የ7 ዓመት ህፃን አስገድዶ ከደፈራት በኋላ አንቆ የገደላት መሆኑን በ8ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ምርመራ መዝገብ ተጣርቶ በመቅረቡ መሰረት መዝገቡ ተመርምሮ በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 539/1/ሐ ላይ ተደራራቢ ክስ በመመስረት የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ተከሳሽ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

ህፃን ሄቨን ላይ እንዲህ ያለ ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ የ25 ዓመት እስራት የተፈረደበት ቢሆንም፤ ቅጣቱን ለማቅለል እና ለማስለቀቅ ይግባኝ የተጠየቅበት አካሄድ የህፃኗን ቤተሰቦች የፍትህ ያለ እንዲሉ እና ብዙዎችንም ያስቆጣ ሆኗል፡፡ 

ህፃን ሄቨን የተፈፀመባት አሰቃቂ መደፈርና ግድያን በተመለከተ የተሰጠው ፍርድ አነስተኛ ነው፣ እንዲሁም በይግባኝ ከእስር ሊወጣ አይገባም በማለት ብዙዎች በዚህ ሰዓት ፍርዱ ይታይልን፣ ፍትህ እንፈልጋለን፣ ፍትህ ለሄቨን የሚል እንቅስቃሴዎችንም እያደረጉ ይገኛሉ።

ጉዳዩን አስመልክቶ የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን ህፃን ሄቨን በተመለከተ በደረሰው ዘግናኝ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ወንጀል የተሰማውን ሀዘን ገልፆ፤ ይህንን አይነት የህፃናት ጥቃት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡

በተፈፀመው ወንጀል ዙሪያም የተሰጠውን ዉሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚኬድበት አግባብ ትክክል ባለመሆኑ ከፍትህ አካላት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ እና እንደሚከታተል ሚኒስቴሩ አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እንዲሁ ትናንት ባወጣው መግለጫው፤ በባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በኩል ድርጊቱ መፈፀሙን መረጃ እንዳገኘ እና ጉዳዪን ካወቀበት ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በቅርበት ሲከታል መቆየቱን አስታውቋል።

ወንጀለኛው የፈፀመው አሰቃቂና ተደራራቢ ወንጀል አሳዛኝና አሰቃቂ ነው ያለው ማህበሩ፤ በተለይ በህፃናት ላይ እንደዚህ ዓይነት ወንጀል ሲፈፀም እጅግ የሚያስከፋና የሚያስቆጣ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱም ወንጀለኛውን በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ብቻ መቅጣቱ እጅግ ያነሰና የግድያ ወንጀሉ ብቻ በራሱ የእድሜ ልክ ወይም የሞት ፍርድ ሊያስቀጣው ሲገባ በ25 አመት ፅኑ እስራት ብቻ ውሳኔ ሰጥቶ ማለፉ ስህተት ነው ብሏል፡፡

የህፃኗ ወላጅ እናትና አባት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ ጭቃኔ ለተሞላበት ድርጊት አስተማሪ እና ቀጪ ፍትህን እንዲሰጥ እየጠየቁ የሚገኝ ሲሆን፤ ብዙዎችም በማህበራዊ ሚዲያው "ሄቨን ልጄ ናት"፣ "ፍትህ ለህጻን ሄቨን"፣ በህጻን ሄቨን ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊ ወንጀል በፅኑ እናወግዛለን በሚል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ይገኛል።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top