ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሄማን በቀለ በታይም መፅሔት የ2024 ምርጥ ልጅ በመባል ተመርጧል።
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ተወልዶ አሜሪካ ነዋሪነቱን ያደረገው ሄማን በቀለ የቆዳ ካንሰር መከላከያ ሳሙና በመፍጠሩ ነው ለዓለም ህዝብ አሳቢ ልብ ያለው ልጅ ለመባል የበቃው።
ሄማን በቀለ ገና የ7 ዓመት ልጅ እያለ ነበር የራሱን የሳይንስ ሙከራዎችን በቤት ውስጥ ማካሄድ የጀመረው። ወላጆቹም ፍላጎቱን በማየት በቅርበት ይከታተሉት ነበር።
በዚህ የጀመረው የሳይንስና የምርምር ፍቅሩ፣ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የ3 ኤም ኩባንያ እና የዲስከቨሪ ትምህርት በፌርፋክስ ካውንቲ ቨርጂኒያ በሚገኘው በውድሰን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባዘጋጀው ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ምክንያት ሆነው።
የ15 ዓመቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሄማን የወጣት ሳይንቲስት ውድደሩንም አሸነፈ፤ የ25 ሺህ ዶላር ተሸላሚም ሆነ።
ሄማን ለዚህ ውጤት ያበቃው ሳሙናዎችን እና ኬሚካሎችን በማዋሐድ የቆዳ ካንሰር የሚከላከል ሳሙና ለመፍጠር ሙከራ በማድረጉ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ ምርት ወደ ገበያ ለመምጣት ዓመታት ሊወስድ ቢችልም፣ ዛሬም በምርምር ላብራቶሪ ጊዜውን ሚያሳልፈው ታዳጊ አንድ ቀን የእኔ ሳሙና በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብሎ ያምናል።
ሄማን ለ2024 የታይም የዓመቱ ምርጥ ልጅ ተብሎ እውቅና እንዲያገኝ የረዳው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ የፈጠራ ስራው እንደሆነ ተነግሯል።
በ4 ዓመቱ ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ኑሮውን አድርጎ የነበረው ሄማን፤ በጠራራማ ፀሐይ ውስጥ የሚሰሩ የጉልበት ሰራተኞችን በየመንገዱ ማየቱ ለቆዳ ካንሰር መድኀኒት ለመፍጠር ምክንያት እንደሆነው ያስታውሳል።
ወላጆቹ እሱን እና እህቶቹን ከቤት ውጭ ብዙ ጊዜ ያለፀሐይ መከላከያ መውጣት የሚያስከትለውን አደጋ ያስረዷቸው ስለነበረ ስለቆዳ ካንሰር ሊያውቅ ችሏል።
ሄማን በኢኮኖሚ ዝቅ ያሉ ሰዎች ከቆዳ ካንሰር እንዴት ነው እራሳቸውን ሚከላከሉት የሚል ጥያቄ በአዕምሮው ይመላለስ ነበር።
በጊዜው ለቆዳ ካንሰር ሕክምና የሚወጣው 40 ሺህ ዶላር የበለጠ ዋጋ ስለሆነ "ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ያለው አንድ ነገር ምንድን ነው፣ ሁሉም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሌለው" በማለት ሄማን ማሰቡን ቀጠለ።
“ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ለማፅዳት ሳሙና እና ውኃ ይጠቀማል።ስለዚህ ሳሙና በጣም ጥሩው አማራጭ ሊሆን ይችላል" በሚል ሳሙና ለመስራት ወሰነ።
ሄማን በቀለ ሳሙናውን በመስራት በባልቲሞር በሚገኘው የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የህዝብ ጤና ትምህርት ቤት በአይጦች ላይ መሰረታዊ ምርምር ሲያካሂድ ቆይተዋል።
አሁን ላይ እንስሳትን በተለያዩ የቆዳ ካንሰር መርፌዎች እና በሊፕይድ የታሰረውን ኢሚኪሞድ የተቀላቀለውን ሳሙና በመቀባት ውጤቱ ምን እንደሆነ ለማየት በዝግጅት ላይ ነው።
እሱን ለመፈተሽ እየተዘጋጀ ቢሆንም ሄማን ገና የሚቀረው ረጅም መንገድ እንዳለ ያውቃል፤ሳሙናን መሞከር ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ባለቤትነት እና የኤፍዲኤ የምስክር ወረቀት ማግኘት በአጠቃላይ አሥር ዓመት ሊወስድ ይችላል።
ቤተሰቦቹን በተለይም ወላጆቹን ለስኬቶቹ መንገድ ስለሆኑ ሁሌም የሚያመሰግናቸው ሄማን፤መምህር የሆኑት እናቱ ሙሉእመቤት እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የሰው ሀብት ስፔሻሊስት የሆኑት አባቱ ወንድወሰን፣ለልጆቻቸው ጥሩ ትምህርትና ኑሮ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ የሚችሉትን አድርገዋል፤ ሊመሰገኑ ይገባል ብሏል።
"ብዙ ሰዎች ሁሉም ነገር ተከናውኗል አልቋል የሚል አስተሳሰብ አላቸው፤ ነገር ግን አሁን ሁሉም ነገር ገና ነው መስራቴን ቀጥላለሁ ዓለማችንን ለማሻሻል እና የተሻለ ቦታ ለማድረግ አዳዲስ መንገዶችን ማሰቤን አላቆምም" ሲልም ሄማን ለታይም መፅሔት ሀሳቡን አካፍሏል።