የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ

5 Mons Ago 607
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አስፍጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ የአራት ዓመት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ ብድር አገልግሎት አቅርቦትን አፅድቋል፡፡

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከለተው ቀርቧል፡-

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ የሚሆንና መጠኑም 2.556 ቢሊየን SDR (የኮታው 850% ወይም ወደ 3.4 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ) የሆነ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መፋለስን መፍታትን እና በግል ዘርፉ ለሚመራ እድገት መሠረት መጣልን አላማው ያደረገውን የመንግሥትን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አፈጻጸም የሚደግፍ የአራት ዓመት የተራዘመ የብድር አገልግሎት አቅርቦት (ECF) አጽድቋል።

የአስፈጻሚ ቦርዱ ውሳኔም ኢትዮጵያ ከባላንስ ኦፍ ፓይመንት ጋር የተያያዙ ፍላጎቶቿን እንድታሟላ የሚረዳትን እንዲሁም በጀቷን የሚደግፈውን የ766.75 ሚሊዮን SDR ወይም 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ የሚሆን ገንዘብ ክፍያ ወዲያውኑ እንዲለቀቅ የሚያስችል ይሆናል።

በአራት ዐመቱ የተራዘመ የብድር አገልግሎት አቅርቦት የሚደገፈው የመንግሥት የኢኮኖሚ ፕሮግራም የግል ዘርፉን እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ ሁለገብ የፖሊሲ ፓኬጅን እንዲሁም የላቀ እና በይበልጥ አካታች የሆነ እድገትን ማምጣት ይቻል ዘንድ ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግን ኢላማው ያደረገ ነው። ማሻሻያው ተጋላጭ በሆኑ ቤተሰቦች/አባዎራዎች ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ለማለዘብ ይቻል ዘንድ የማህበራዊ ሴፍቲ ኔቶችን ማጠናከርም የመንግሥት የማሻሻያ ፕሮግራም አንድ ወሳኝ ክፍለ አካል ነው።

ቁልፍ የሚባሉት ፖሊሲዎችም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

1) ውጫዊ ኢሚዛናዊንትን ለመፍታት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማስታገስ በገበያ ወደሚወሰን የምንዛሪ ዋጋ መሄድ፤

2) የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍን በማዘመን የዋጋ ግሽበትን መዋጋት፤

3) የሀገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮችን በማሰባብሰብ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሕዝባዊ ወጪዎች ማዋል፤

4) ከውጪ አበዳሪዎች ጋር የሚደረጉ ወቅታዊ የእዳ ሪስትረክቸሪንግ ስምምነቶችን በመፈጸም ጭምር የእዳ አከፋፈል ዘላቂነትን መመለስ እንዲሁም

5) ወሳኝ የሆኑ የማክሮ ፋይናንሺያል ተጋላጭነቶችን ለመቀነስ የመንግሥት ኢንተርፕራይዞችን የገንዘብ አቋም ማጠናከር።

ፕሮግራሙ ከልማት አጋሮች የሚገኝ ተጨማሪ የገንዘብ አቅርቦትን በማፋጠን እንዲሁም በመካሄድ ላይ ያለው የእዳ ሪስትረክቸሪንግ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ ማዕቀፍ በመስጠት ረገድ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top