በ2016 ዓ.ም የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃን በማጎልበት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ሥድስተኛ ዙር ሶስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
የሐረሪ ጉባኤ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀማቸውን በጉባዔው ላይ አቅርበዋል።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ በባህል፣ ቅርስና በሐረሪ ቋንቋ ጥበቃና የማጎልበት ስራዎች በሰፊው መከናወናቸው በጉባኤው ተመላክቷል።
በተለይ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ፣ የባህል እሴቶችን የመጠበቅና የማበልፀግ፣ በዓመቱ የባህላዊና ታሪካዊ ሥነ ሥርዓቶችና በዓላት ነባር ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲካሄዱ ከማድረግ አንፃር የተደረጉ የክትትል እና ድጋፍ ስራዎች በመድረኩ ላይ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃን በማጎልበት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አቶ ኦርዲን መድረኩ ገልጸዋል።
በተለይ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የሹዋሊድ በዓል በማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ ብሎም የሐረሪ ቋንቋን ከማሳደግና ደረጃን ከማሻሻል አንፃር የተዘጋጁ የትርጉም መተግበሪያዎች አበረታች መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የጉባኤው አባላት በበኩላቸው፤ በቀረበው ሪፖርት ላይ በሰጡት አስተያየት በበጀት አመቱ በዘርፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።
የተጀመሩ ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀዉ ሊከናወኑ ይገባል ያሉት አባላቱ፤በተለይ ጉባዔው አስፈፃሚ ተቋማት ያካሄዷቸውን ተግባራት ከመከታተል አንፃር ጥሩ የሚባል ክትትል ዕና ድጋፍ ማድረጉን በመጠቆም የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ጉባዔው በክልሉ ህገ መንግስት የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሠረት በማድረግ በይበልጥ ጠንካራ ህግ ማውጣትና የክትትል ስራዎችን መስራት እንደሚገባም መነሳቱን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ጉባዔው ከመከረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
በተጨማሪም የ2017 ዓመት የሐረሪ ጉባዔ ፣ የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የክልሉ ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ዕቅድ ቀርቦ በአባላቱ አስተያየት ከተሰጠበትና ከተመከረበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።