የታዳጊ ሀገራትን ዘላቂ ልማት ለመደገፍ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለፁ፡፡
አምባሳደሩ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው በአራተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፤ ኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆነውን ዓመታዊ በጀቷን ለዘላቂ ልማት ግብ እንደምትጠቀም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የታዳጊ ሀገራትን ዘላቂ ልማት ለመደገፍ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዋና ዋና የልማት ግቦች ላይ ለውጥ እያመጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ በትምህርት፣ ጤና፣ በማህበራዊ፣ ደህንነትና በሌሎችም ዘርፎች ኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣታን ገልጸዋል።
ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ምሳሌ ሊሆን የሚችል ስራ በአረንጓዴ አሻራ እየተገበረች ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በተመረጡ የልማት ግቦች የፋይናንስ አቅርቦትን ለማመቻቸት ታቅዶ በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ፤ ያደጉ ሀገራትና አበዳሪ ተቋማት ለሁሉም የሚጠቅም የገንዘብ አቅርቦት ስርዓት ሊያመቻቹ እንደሚገባ ተገልጿል።
በውይይቱ የፋይናስ አቅርቦት አናሳ መሆን ታዳጊ ሀገራት ዘላቂ ልማት ላይ እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።
ታዳጊ ሀገራት ያለባቸው ከፍተኛ የእዳ ጫና ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰውም ነው የተገለፀው።
የታዳጊ ሀገራትን ዘላቂ ልማት ለመደገፍ የፖለቲካ ቁርጠኝነትም አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ውይይቱ ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዚህ ውይይት የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች በቀጣይ አመት በስፔን በሚካሄደው የተመድ ጉባኤ ለተፈጻሚነታቸው ምክክር እንደሚደረግባቸው ታውቋል።
በአዝመራው ሞሴ