በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

9 Days Ago
በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የርዕሰ መሥተዳድሩ የመሰረተ-ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ ገለፁ፡፡

በክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር የተቋቋመው ግብረ-ኃይል በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግሥት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ሂደት ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጋር ገምግሟል፡፡

በዚህም የአስፋልት መንገድ የሥራ እንቅስቃሴን ጨምሮ የጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል እየተከናወነ ያለውን ሂደትና የመገጭ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ግምገማ ተደርጎበታል፡፡

በግምገማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የርዕሰ መሥተዳድሩ የመሰረተ-ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በአጭርና ረዥም ጊዜ በዕቅድ በተያዘው መሰረት በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸው፤ የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የመገጭ ግድብ አዲሱ ተቋራጭም በክረምቱ አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከአዘዞ -ዐርበኞች ዐደባባይ የአስፋልት መንገድ ሥራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የተቋራጩ ውል ተሰርዞ ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ከተሰጠ በኋላ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለታቸውን የጎንደር ከተማ ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡

ከስትራክቸር ሥራው ጎን ለጎን የአስፋልት ንጣፍ ሥራው ከፍተኛ መሻሻል አለው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመገጭ ግድብ ለአዲስ ተቋራጭ ውል መሰጠቱን እና በ1 ዓመት ከ6 ወራት ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top