የህፃናትን ጥቃት መከላከል የሚያስችል የህፃናት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ገቢራዊ ተደርጓል፡- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

7 Days Ago
የህፃናትን ጥቃት መከላከል የሚያስችል የህፃናት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ገቢራዊ ተደርጓል፡- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
የህፃናትን ጥቃት መከላከል የሚያስችል የህፃናት መረጃ አያያዝ ሥርዓት ገቢራዊ መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
 
የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
 
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ በመቶ ቀናት የግምገማ መድረክ በማህበራዊ ጉዳዮች የተነሱ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
በዚህም ባለፉት አስር ወራት በሕገ ወጥ መንግድ የተሰደዱ ዜጎችን የመመለስና የህፃናትን ጥቃት መከላከል የሚያስችሉ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
 
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
 
በዚህም 200 የሚሆኑ ልጆች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ልጆች የሀገራቸውን ማንነት ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ስርዓት እንዲጠናከር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ በምትከተለው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በውጭ አገራት ታስረው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
በዚህም ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኦማን እና ሱዳን 90 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ የተቻለ ሲሆን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
 
በተለይም የወጣቶችን ሕገ ወጥ ስደት በመግታት በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ በተግባር ለማሳየት ብሔራዊ የድርጊት መርሐ-ግብር ተቀርፆ ስራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡
 
የህፃናትን ጥቃት በመከላከል ረገድም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ የህፃናት መረጃ አያያዝ ስርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
 
የህፃናት መረጃ አያያዝ ሥርዓቱ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎችም ይተረጎማል ብለዋል።
 
በቀበሌዎች የማህበረሰብ ጥምረት በማቋቋም የህፃናትን የጥቃት ተጋላጭነት መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
በዚህ የተቀናጀ አሰራርም 1 ሺህ 40 ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናትን ወደ ጎዳና ሕይወት ከመውጣት ታድገናል ሲሉ ተናግረዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top