የመጻሕፍት ተማሪ ጥምርታ 1 ለ 3 ደርሷል፡- ትምህርት ሚኒስቴር

7 Days Ago
የመጻሕፍት ተማሪ ጥምርታ 1 ለ 3 ደርሷል፡- ትምህርት ሚኒስቴር
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ10 ወራት የትምህርት ሴክተር አፈጻጸምን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የትምህርት ዘርፉን በሁሉም ረገድ ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ውጤትም እየታየባቸው ይገኛል፡፡
 
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች ሐብቶችን በማሰባሰብ 5 ሺህ 873 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የ14 ሺህ 791 ትምህርት ቤቶች ጥገና ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
 
የትምህርት ፋሲሊቲዎችን ለማሟላት በተደረገው ጥረትም 11 ሺህ 642 የመማሪያ ክፍሎች እና 7 ሺህ 487 ቤተ መጻሕፍት 1 ሺህ 821 ቤተ ሙከራዎች ለተሻለ አገልግሎት እንዲበቁ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
 
45 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ 22.7 ሚሊዮን መጻሕፍት መታተሙን፣ 20.6 ሚሊዮን መጻሕፍት ለክልሎች፣ 2 ሚሊዮን ለግል ትምህርት ቤቶች መከፋፈሉን ገልጸው፣ ይህም የመጻሕፍት ተማሪ ጥምርታ 1 ለ 3 እንዳደረሰው አውስተዋል፡፡ በቀጣይም ጥምርታውን 1 ለ 2 ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
 
የትምህርት ቤቶችን መረጃ በዘላቂነት ለመያዝም 56 ሺህ 618 ትምህርት ቤቶች መረጃዎቻቸውን በፖርታል ማስገባታቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡
 
የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራም 7.88 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
 
የ2016 ትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን በተመለከተም ድህረ ብሔራዊ ፈተና ትንተና የተካሄደ ሲሆን፤ የዘንድሮው ፈተና በወረቀት እና በኦንላይን እንዲሰጥ መወሰኑንም አስታውሰዋል፡፡
 
ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንዳሉት፤ የሪሜዲያል ፈተና አሁን እየተሰጠ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ዝግጅትም ተጠናቆ ተማሪዎች በኦንላይን ለመፈተን ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡
 
ሌላው የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል የሚሠራው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ 62 ሺህ ለሚሆኑ የትምህርት ቤት አስተዳደር አካላት እና መምህራን ሙያቸውን የሚያሻሽሉበት ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
 
በክረምቱም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የዝግጅት እና እድሳት ሥራ እንደሚሰራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን የዩንቨርሲቲ ትምህርት ቀደም ብሎ በመስከረም ውስጥ እንዲጀመር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top