የኪንታሮት በሽታ (hemorrhoids)

7 Mons Ago 1177
የኪንታሮት በሽታ (hemorrhoids)

የኪንታሮት በሽታ (hemorrhoids) በፊንጢጣ ላይ የሚገኙ ደም መላሽ የደም ስሮች ሲያብጡ የሚፈጠር በሽታ ሲሆን፣ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኝ ቢሆንም ከ45-65 ዓመት ባሉት ሰዎች ላይ በብዛት እንደሚከሰት የሕክምና ባለሞያዎች ያስረዳሉ፡፡

የኪንታሮት በሽታ በዋናነት በሁለት ይከፈላል፡፡ ውጫዊ ኪንታሮት (external hemorrhoids) በውጨኛው የፊንጢጣ ክፍል ላይ የሚከሰት ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ሕመምም (Pain) ያስከትላል፡፡

ሌላው ውስጣዊ ኪንታሮት (internal hemorrhoids) በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ሕመም አይኖረውም፤ ይህ የኪንታሮት ዓይነት 4 ደረጃዎች (grades) አሉት።

አንደኛ ደረጃ ይህ ደረጃ በፊንጢጣ፡- ግድግዳ ላይ እብጠት ሲኖር እንዲሁም እብጠቱ በዋናነት በስተ ግራ፣ በፊት ለፊት እና በስተኋለኛው የፊንጢጣ ግድግዳ ላይ ይከሰታል፡፡

ሁለተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ የእብጠቱ መጠን ጨምሮ ለሽንት ሲቀመጡ በሚኖር ማማጥ እባጩ ወደ ውጪ ሲወጣ እና በራሱ ጊዜ ወደ ውስጥ ሲመለስ ነው፡፡

ሦሥተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ እባጩ ለሽንት ሲቀመጡ ወደ ውጪ ይወጣና በራሱ ስለማይመለስ የግድ በእጅ መመለስ ሲፈልግ ነው፡፡

አራተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ እባጩ ላይመለስ በፊንጢጣ ይወጣና ይቀራል፡፡

አጋላጭ ሁኔታዎች (risk factors)

የሆድ ድርቀት፣ አነስተኛ የፋይበር መጠን ያላቸው ምግቦችን ማዘውተር (ፓስታ፣ ማኮሮኒ፣ ነጭ ዳቦ …)፣ በቂ ውሃ አለመጠጣት ናቸው፡፡ በተጨማሪም

👉 የትልቁ አንጀት ካንሰር፣
👉 ሽንት ቤት ተቀምጦ ለረጅም ጊዜ ማማጥ፣
👉 ረጅም ጊዜ የቆየ ተቅማጥ (chronic diarrhea) ፣

ለኪንታሮት ህመም የሚያጋልጡ ናቸው፡፡

የኪንታሮት በሽታ ምልክቶች በርካታ ሲሆኑ፣ ከነዚህ መካከል፡-

👉 ሕመም የሌለው ከፊንጢጣ የሚፈስ ደማቅ ቀይ ደም፣
👉 በፊንጢጣ አካባቢ ማሳከክ፣
👉 ከፊንጢጣ የሚወጣ ሥጋ መሳይ እባጭ፣
ይገኙበታል፡፡

የኪንታሮት በሽታ የሚያስከትላቸው ችግሮች

ኪንታሮቱ ውስጥ የደም መርጋት (thrombosis)ና ከፍተኛ ሕመም፣ የፊንጢጣ ወጥቶ አለመመለስ፣ (irreducible)፣ መበስበስ (Necrosis)፣ መመርቀዝ (infection) እና መግል መቋጠር፣ ያልተለመደ የሰውነት ክፍተት (fistula)፣ የሰውነት መሰንጠቅ (fissure)፣ ሰገራን አለመቆጣጠር (Incontinence) እና በአብዛኛው የተለመደ ባይሆንም የደም ማነስ ሊያስከትል ይችላል፡፡

የኪንታሮት ሕክምና

በመጀመሪያ ሕመሙ ያለበት ሰው እንደማንኛውም ሕመም ወደ ሐኪም ቤት ሄዶ ለመታከም ፍርሃትን ማሰወገድ እንደሚጠበቅበት ሐኪሞች ደጋግመው ይመክራሉ፡፡

በመቀጠል በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን (አትክልትና ፍራፍሬ..) መመገብ፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድ፣ ለብ ባለ ውሃ ጨው ጨምሮ 20- 30 ደቂቃ በቀን ሁለቴ ወይም ሦሥቴ መዘፍዘፍ (በበረዶም ሊሆን ይችላል)፣ ሁሌም ከተፀዳዱ በኃላ በንጹሕ ውሃ መታጠብ፣ ሻካራ የመፀዳጃ ወረቀቶችን አለመጠቀም እና የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒት መጠቀም እና የሚቀባ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት መጠቀም ይገኝበታል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ብቻ ሕመሙ ሊሻሻልና ሊጠፋ ይችላል፡፡ በእነዚህ ሕክምናዎች ካልተስተካከለ ቀለል ያለ ቀዶ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

መከላከያ መንገዶቹ

በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድ እና የሆድ ድርቀትን ማስወገድ፣ ጊዜውን ሳያሳልፉ ወደ መጸዳጃ ቤት መሄድ፣ መፀዳጃ ቤት ለረጅም ሰዓት አለመቀመጥ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በሜሮን አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top