"በመፅሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኑና እንዋቀስ ይላል፤የእኛም የእርስ በእርስ መነጋገር አስፈላጊ ነው"- ፓስተር ጻዲቁ አብዶ

7 Mons Ago 824
"በመፅሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኑና እንዋቀስ ይላል፤የእኛም የእርስ በእርስ መነጋገር አስፈላጊ ነው"- ፓስተር ጻዲቁ አብዶ
በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር" የሚል ቃል አለ፤ ይህን መሰረት ብናደርግ እኛም እርስ በእርሳችን መነጋገራችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳየን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት ፕሬዚዳንትፓስተር ጻዲቁ አብዶ ገለጹ።
 
የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ ፤በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጥበበኞች ዘመኑን የሚያውቁ (የሚመክሩ) ‘ይሳኮር’ የሚባሉ ወገኖች እንደነበሩ ተናግረዋል።
 
"ምክር በሰው ልብ እንደጠሊቅ ውኃ ነው፤አዕምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል"ይላል መፅሐፉ የሚሉት ፓስተር ጻዲቁ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም የሚያካትት በመሆኑ ያላግባቡን ጉዳዮች ላይ በግልጽ መወያየት አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
 
"ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዘመናት በጎውንም ክፉውንም አይተናል፤አሁን ላይ ያሉ አለመግባባቶችን ሁሉ ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት እና ሀገርን በማስቀደም ልንመክር ይገባል" ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ያላት የህዝብ ብዛትም ሆነ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ለጥፋትም ሆነ ለልማት እንደሚሆን በመግለጽ፤ለሀገር እና ለሰላም ሲባል ከራስ ወዳድነት ስሜት መውጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
 
በሐይማኖት አስተምህሮ ውስጥ ጉባዔዎች ስለመኖራቸው የገለጹት ፓስተር ጻድቁ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ያላግባቡ ጉዳዮች በጉባዔ ታይተው አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ መደረጋቸውን አመላክተዋል፡፡
 
“ችግሮቻችን ምን እንደሆኑ በግልጽ መነጋገር አለብን፤ችግሮቻችንን ካወቅን ለመፍትሄ መቀመጡ መልካም ነው” የሚሉት ፓስተር ጻዲቁ፤ የሃሳብ ልዩነቶችን በኃይል ለማስተናገድ መሞከር ለየትኛውም አካል አይበጅም ይላሉ፡፡
 
"ኢትዮጵያ ሀገር ሆና እንድትቀጥል የበደሉንን ሰዎች ይቅር ልንል ይገባል፤ ሰላም ካለ ብልጽግና ይቀጥላል፤ ክፉውን ትተን ወደፊት መራመድ ያስፈልገናል" ብለዋል ፓስተር ጻዲቁ፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top