የቃል እና የፅሁፍ ማስረጃ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል?
አንዳንድ ሰዎች የዋህ ናቸው። ከነዚህ የዋሆች መሀል አቶ ጌታሁን አንዱ ይመስሉኛል። ምክንያቱም ሰኔ 5 ቀን 1997 ዓ.ም ለአቶ ታደሰ መኪና ገዝተን አብረን እስክንጠቀምበት ለጊዜው በአደራ አንተ ጋር ይቀመጥልኝ ብዬ በምስክር ፊት መቶ ሰማንያ ሺህ ብር ቆጥሬ ሰጠሁት ነው የሚሉት።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቶ ጌታሁን ገንዘቡን መልስልኝ ብለው ጠየቁት። አቶ ታደሰ ግን እንደሳቸው የዋህ አልነበረምና አልመልስም አላቸው። ይሄኔ አቶ ጌታቸው ‘‘ሕግ ባለበት አገርማ ብሬ ቀልጦ አይቀርም’’ ብለው አቶ ታደሰ ላይ ‘‘በአደራ የሰጠሁትን 180 ሺህ ብር ከነወለዱ ይመልስልኝ’’ የሚል ክስ አቀረቡ።
የክሱ መጥሪያ የደረሳቸው አቶ ታደሰ ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጡት መልስ አቶ ጌታቸው በአደራ የሰጧቸው ገንዘብ አለመኖሩንና በሕግ ተቀባይነት ያለው ማስረጃም አለማቅረባቸውን ጠቅሰው ተከራከሩ።
ፍርድ ቤቱም የአቶ ጌታቸውን ምስክሮች አዳመጠና አቶ ታደሰ የተጠቀሰውን ገንዘብ መቀበላቸውን ስላረጋገጠ በየአመቱ የሚሰላ ሕጋዊ ወለዱ 9% ጨምረው የተቀበሉትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ወሰነባቸው። ነገሩ በዚህ ቢቋጭ ጥሩ ነበር ሆኖም ግን ቀጠለ።
አቶ ታደሰ ይግባኝ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት ስላላገኙ በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ይታረምልኝ ሲሉ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቀረቡ።
አቤቱታውም በአደራ ገንዘቡን መቀበሌን የሚያረጋግጥ በሕግ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ ሳይቀርብብኝ ገንዘቡን እንድከፍል መወሰኑ ከሕጉ አግባብ ውጭ ነው የሚል ነበር።
አቶ ጌታሁንም መጥሪያ ደርሷቸው ለሰበር ችሎቱ የስር ፍቤት የፈጸመው የሕግ ስህተት የለም ስለዚህ ውሳኔው ሊፀና ይገባል ሲሉ መልስ ሰጡ። ሰበር ችሎቱ የተከራካሪዎችን የፅሁፍ እና የቃል ክርክር እና አቤቱታ የቀረበበትን ውሳኔ ከሕጉ ጋር አገናዝቦ መርምሮ የሰጠው የመጨረሻው አስገዳጅ ፍርድ በየዋህነት በገንዘብ ጉዳይ ላይ ያልተጠነቀቅናቸው የሕግ ጉዳዮች ሚያስከፍሉትን ዋጋ የሚያሳይ ነው።
ከአምስት መቶ ብር በላይ
የዋህነትና ሰዎችን ማመን መልካም ነው። በገንዘብ ጉዳይ ግን መጠንቀቁ ይመከራል። በብድር ወይም በአደራ ገንዘብ ስትሰጥ ከብር 500 በላይ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ ይሄ ነው። ገንዘቡን የምንሰጠው ሰው የፈለገ የቅርብ ጓደኛችን ቢሆን የእናትም ልጅ ቢሆን መጠኑን ጠቅሰን ገንዘቡን እንደሰጠነውና መስጠታችንንም ቢያንስ ሁለት ምስክሮች ማየታቸውን ገንዘቡ መቼ እንዲመለስ እንደተስማማችሁ የሚጠቅስ ውል መፃፍና አበዳሪ/አደራ ሰጪም ሆነ ተቀባይ እንዲሁም ምስክሮች የፈረሙበትን ውል ለማስረጃ መያዝ ያስፈልጋል። ወረቀት የያዘውን ስለማይለቅና እንደ ሰው ቃሉን ስለማያጥፍ በሕግ ፊት ከምስክር ቃል በላይ ይታመናል።
ብድሩን እንዴት ማስረዳት ይቻላል
እንደ አቶ ታደለ ገንዘቡ የተሰጠው ሰው አላውቅም ብሎ ቢክዳችሁና ፍርድ ቤት ብትሄዱ ከ500 ብር በላይ የገንዘብ ብድርን ወይም አደራን ተበዳሪው ወይም አደራ ተቀባዩ ከካደ በፅሁፍ የሰፈረ የብድር ውል ወይም የአደራ ውል ካላቀረብን በምስክር ብቻ ለማስረዳት አንችልም።
ያለው አማራጭ ፍርድ ቤቱ ፊት ተከሳሹ ቀርቦ ምሎ ገንዘቡም አለመውሰዱን እንዲያረጋግጥ መጠየቅ ብቻ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ፈጣሪንም ሕግንም ስለማይፈራ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ ግጥም አድርጎ ነው ሚምለው። ፍርድ ቤት ደግሞ እንደምትጠይቀው የውል ግዴታ አይነት ሕጉ ተገቢ ያለውን ማስረጃ ካላቀረብክለት ምንም ሊያደርግልህ አይችልም።
ገንዘብ በአደራ ስትሰጡ የታሸገ ከሆነ ከ500 ብርም በላይ ቢሆን በምስክር ፊት ከሰጣችሁ ምስክሮቹን አቅርቦ ማሰረዳት ይችላል። ሆኖም ቆጥራችሁ ከሰጣችሁት (ገንዘቡ ካልታሸገ)በሕጉ እንደ አላቂ የገንዘብ ብድር ስለሚቆጠር የተፃፈ ውል ከሌለ ገንዘባችሁን በፍርድ ቤት ከሳችሁ ማስመለስ አይቻልም። ምክንያቱም ሕጉ ከተጠቀሱት ማስረጃዎች ውጭ ሌላ አይነት ማስረጃ አይቀበልም።
የትዳር አጋርን በሚመለከት
በተጨማሪ ከ500 ብር በላይ ስታበድሩም ሆነ ስትበደሩ ወይም ዋስ ስትሆኑ የፅሁፍ ውል ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተሻሻለው የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ መሰረት ካገባችሁ ሚስት ባሏን ባል ሚስቱን በውሉ መስማማቷ/ቱን በውሉ ላይ በመፈረም ማረጋገጥ አለባ/በት። ካልሆነ በውሉ ላይ ስምምነቱን ያልገለፀው ተጋቢ ክስ አቅርቦ ውሉን ማስፈረስ ይችላል።
አቶ ጌታቸውም በአደራ ቆጥሬ ሰጠሁ ያሉት ብራቸው እንደወጣ የቀረው በዚህ የተነሳ ነው።
የሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ
ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከላይ የጠቀስኳቸውን የገንዘብ አደራን እና ብድርን የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች በመጥቀስ ‘‘አቶ ታደሰ ገንዘቡን አልወሰድኩም ብለው ከካዱ መቅረብ ያለበት የፅሁፍ ውል ነው።
ይህ የፅሁፍ ውል ስላልቀረበና አመልካች ለጉዳዩ ተገቢነት ያለው ማስረጃ ባላቀረቡበት በምስክር ብቻ የስር ፍርድ ቤት 180 ሺውን ወስደዋልና ይክፈሉ ብሎ በመወሰኑ የሕግ ስህተት ስለፈፀመ ውሳኔውን ሽሬዋለሁ’’ በማለት አቶ ታደሰ በአደራ ተቀበሉ ተብለው የተከሰሱበትን 180 ሺህ ብር ሊከፍሉ የሚችሉበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ብሎ የወሰነው።
ውሳኔው የሰበር ውሳኔዎች ቅፅ 12 ላይ ታትሞ ወጥቷል።
ለማንኛውም መሰል ጉዳዮች ሲያጋጥሙን አሁን ያለውን መተማመን ብቻ ሳይሆን በኋላ ሊያጋጥም የሚችለውን መካካድ በማሰብ ሕጋዊ ጉዳዮችን መጠንቀቅ ይመከራል።