"በነፃ የስልክ ጥሪው የምናገኘው መረጃ የአገልግሎት አሰጣጣችንን እንድናሻሽል ግብዓት ሆኖናል"፡- የኦሮሚያ ጤና ቢሮ
"አገልግሎቱ ጊዜ እና ገንዘባችንን ቆጥበን አስፈላጊውን የጤና መረጃ እንድናገኝ አስችሎናል"፡- ተጠቃሚዎች
*********************
የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ በርካታ የጤና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ መከላከልን ቅድሚያ ትኩረቱ ያደረገው ቢሮው በሽታ ሲከሰትም አስፈለጊውን ርብርብ እያደረገ የሕብረተሰቡን ጤና እየጠበቀ ይገኛል፡፡
ሕዝብረተሰቡ ለጤናው ለሚያደርገው ጥንቃቄ ዋናው መረጃ በመሆኑ በየዕለቱ የመረጃ ተደራሽነትን ተግባራዊ በማድረግ አርዓያ የሚሆን ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡
ቢሮው የጤና ትምህርቶችን እና መረጃዎችን ተደራሽ ከሚያደርግባቸው መንገዶች መካከል 6955 ነፃ የስልክ ጥሪ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡
በዚህ ነፃ የስልክ ጥሪ ሦስት አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው የጤና ትምህርት ሲሆን ሕብረተሰቡ ማንኛውንም ከጤና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ጠይቆ ምላሽ የሚያገኝበት ነው፡፡
ሌላው የጤና መረጃ ነው፤ ሕብረተሰቡ ደውሎ የፈለገውን አገልግሎት የሚያገኝባቸው የጤና ተቋማት በቅርቡ የት እንደሚገኙ ጠይቆ መረጃ የሚያገኝበት ነው፡፡
ሦስተኛው የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎቹን የሚያቀርብበት ነው፤ በክልሉ ባለው በየትኛውም የጤና ተቋም ሊገለገል ሄዶ አጥጋቢ ምላሽ ያላገኘ ተገልጋይ በዚህ ነፃ የስልክ መስመር ደውሎ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል፡፡
ሲስተር ሰዓዳ አሊ በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የጤና ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በዚህ ጉዳይ ላይ ለኢቢሲ ሳይበር እንደተናገሩት፤ ይህ ነፃ የስልክ መስመር የጀመረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ነበር፡፡
በኮቪዲ ወረርሽኝ ጊዜ 24 ሰዓታት አገልግሎ ይሰጥ እንደነበር የገለጹት ሲስተር ሰዓዳ፤ ሁሉም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ቀን ከሌሊት ሲታትሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በዚያ ጭንቅ ሰዓት ሕብረተሰቡ የሚያማክረውን ሰው በሚፈልግበት እኩለ ሌሊት ጭምር መረጃ ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም በጣም አስፈሪ የነበረውን ወረርሽኝ ለማለፍ በነፃ ስልክ መስመሩ የተሰጠው መረጃ ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል፡፡
ኮቪድ ወረርሽ መሆኑ ካለፈ በኋላ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኮንትራቱን ጨርሶ አገልግሎቱ እንደተቋረጠም ያስታውሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ይላሉ ሲስተር ሰዓዳ፣ "ይሁን እንጂ አገልግሎቱ በጣም አስፈላጊ ስለነበር እንደ ቢሮ አገልግሎቱን የምናስቀጥልበትን መንገድ ከተወያየን በኋላ ጉዳዩን ለክልሉ መንግሥት አሳውቀን፣ መንግሥትም የአግልግሎቱን አስፋላጊነት አምኖበት በጀት እና የሰው ኃይል ፈቀደልን" ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ አሁን ሰባት አባላት ባሉት አንድ ቡድን የሚመራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀን በትንሹ እስከ 200 ሰዎች ከፍ ሲልም ከ1 ሺህ እስከ 1 ሺህ 500 ሰዎች እየደወሉ የፈለጉትን ጤና ነክ መረጃ በነፃ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡
ኦፕሬተሮቹ የጤና ባለሙያዎች በመሆናቸው አብዛኛውን መሰረታዊ የጤና መረጃ ራሳቸው እንዲሰጡ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል፡፡
አግልገሎቱ የሚሰጠው በመደበኛ የሥራ ሰዓት መሆኑን እና ህዝብ በአደባባይ የሚሳተፍባቸው ትላልቅ ሁነቶች ሲኖሩ እንዲሁም ወረርሽኝ ሲከሰት የ24 ሰዓት አግልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡
የጤና ተቋማት ላይ በሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ላይም ሕዝቡ ያለውን ቅሬት በቀጥታ ነፃ የስልክ መስመሩ እያቀረበ መሆኑን እና ከዚያ በተገኙ ግብዓቶች መሰረት በርካታ የአግልግሎት ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱን እየሰጡ ያሉ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ ሕዝቡ ነፃ የስልክ መስመሩን ተጠቅሞ በጤና ዙሪያ ያለውን ማንኛውንም ጥያቄ እየጠየቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለጠየቁት ጥያቄ በቂ ምላሽ እና እርካታ በማግኘታቸው ደውለው የሚያመሰግኑ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ኢቢሲ ሳይበር ስለ አገልግሎቱ የጠየቃቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ገንዘባቸውን እና ጊዜያቸውን ቆጥበው አስፈላጊውን የጤና መረጃ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡
ከምዕራብ ሐረርጌ አቶ ሀምዲ ቶፊቅ፣ ከምዕራብ ሸዋ አቶ ዳኜ ዱጋ፣ ከምሥራቅ ሸዋ አቶ መስፍን አበራ አገልግሎቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ በነፃ ስልክ አገልግሎቱ ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለአካባቢያቸው የሚተርፍ የጤና መረጃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ