"ዘንድሮ በኦንላይን የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ኮምፒውተሮች ይከናወናል"፡- ሀገር አቀፍ ትምህርት፣ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት

30 Days Ago
"ዘንድሮ በኦንላይን የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ኮምፒውተሮች ይከናወናል"፡- ሀገር አቀፍ ትምህርት፣ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት

ዘንድሮ በወረቀት ከሚሰጠው ፈተና ጎን ለጎን ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን (በበይነ መረብ) የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ኮምፒውተሮች እንደሚከናወን የሀገር አቀፍ ትምህርት፣ ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ገለጸ።

አንዳንድ ወላጆች "በኦንላይን (በበይነ መረብ) ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና የመፈተኛ ኮምፒውተር እንድናቀርብ ተጠይቀናል" ማለታቸውን ተከትሎ፤ኢቢሲ ሳይበር የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ስለጉዳዩ ጠይቋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በምላሻቸው፤ይህንን በሚመለከት ለትምህርት ቤቶች የተላለፈ መልዕክት አለመኖሩን እና ወላጆች መጠየቃቸውም ተገቢ አለመሆኑን ገልጸው፤ፈተናው መንግስት በሚያዘጋጀው አቅርቦት ይከናወናል ብለዋል።

ተማሪዎች ለፈተና ሲመጡ የሚጠበቅባቸው አንብቦ እና በቂ ዝግጅት አድርጎ የተመዘገቡበትን መታወቂያ ይዞ መምጣት ብቻ እንደሆነም አመላክተዋል።

ሆኖም ግን ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ተማሪዎች የግል ኮምፒውተሮቻቸውን ለፈተናው መጠቀም ከፈለጉ እንደማይከለከሉ ነው የገለጹት።

“የወረቀት ህትመት ወደ መጠናቀቁ ነው። በኦንላይን (በበይነ መረብም) ፈተና የሚወስዱ ተፈታኞች ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ የልምምድ ጊዜ እየተሰጣቸውም ይገኛል። በዚህም ለአጠቃቀም ምቹ እንደሆነ ያገኘነው ግብረ መልስ አሳይቶናል" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

ይህ አዲስ የኦንላይን (የበይነ መረብ) ሥርዓት በራሳቸው የይለፍ ቃል(ፓስወርድ) የተዘጋጀላቸው እንደሆነ እና በስልክ እና በኮምፒውተር በማንኛውም ጊዜ እና ሰዓት መለማመድ እንዲችሉ ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ሁሉንም ተፈታኞች በኦንላይን (በበይነ መረብ) እንዲፈተኑ ለማድረግ የመሰረተ ልማት አለመሟላት እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል ዘንድሮ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ብቻ የሚጀመር ይሆናል ነው ያሉት።

ለዘንድሮው ፈተና 156 የኮፒውተር ባለሙያዎች ሰልጥነው በክልሎች ስልጠና እንዲሰጡ መሰማራታቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኔትወርክ እና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዳይገጥም ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው ፈተና ልምዶችን በመያዝም፤ በሚቀጥሉት ከ3 እስከ 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን (በበይነ መረብ) የመስጠት ዕቅድ መኖሩንም አመላክተዋል፡፡

የዘንደሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 7/2016 ዓ.ም ቀን ድረስ እንደሚሰጥ መገለጹ የሚታወስ ነው።

በሜሮን ንብረት

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top