"ጋዜጠኛ በንፁህ ኅሊናው ሚዛናዊ የጋዜጠኝነት ሥራን መሥራት እንጂ ሙያውን የሚያራክስ ነገር መሥራት የለበትም፤ አሁን እንደወረርሽኝ የወረረን የጋዜጠኝነት ሙያን የሚያራክስ ድርጊት ነው፤ ጋዜጠኛ በድለላ እና በጉቦ አይሠራም" በማለት ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ክቡርነት ይናገራል።
"ጋዜጠኝነት አልጋ በአልጋ አይደለም። ድፎ ዳቦ ተሆኖ ነው የሚሠራው፤ ከላይ እሳት፤ ከስር እሳት ነው" በማለት በራሱ ኖሮ ያየውን የጋዜጠኝነትን ፈተናዎችም ይገልጻል።
የጋዜጠኝነት ሥራውን በሬዲዮ ላይ እንደመጀመሩ ሬዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደራሽነቱም በተደማጭነቱም ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበር ይናገራል።
ከሀገራችን ምርጥ ገጣሚያን እና አጫጭር ልብወለድ ጸሐፊዎች አንዱ ነው። በጋዜጠኝነት፣ በመምህርነት እና በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት ሀገሩን ያገለገለ ሲሆን፣ ብዙዎች የሚያውቁት በደራሲነቱ ነው።
"በድርሰቶቻቸው ኢትዮጵያን በሙሉ ለማሳየት እና ለመዳሰስ ከሞከሩት ጥቂት ደራሲያን መካከል አንዱ ነው" በማለት እንዴት በድርሰቶቹ የኢትዮጵያን መልክ ለማሳየት እንደሞከረ የኢትኖግራፊ ተመራማሪው አፈንዲ ሙተቂ ይመሰክርለታል።
በመጻሕፍቱ አማካኝነት ተደራሲያኑ ባሉበት ሆነው የኢትዮጵያን ባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የኪነ-ህንጻ፣ የሙዚቃ፣ የሥነ-ቃል፣ የማኅበራዊ ህይወት፣ የመልክዓ ምድር እና የሥነ-ጥበብ (fine art) ሐብቶች በምናብ እንዲዳስሱ እንዳደረገም ይነገርነታል።
የዛሬው ባለታሪካችን ጋዜጠኛ እና ደራሲ አበራ ለማ የተወለደው በ1943 ዓ.ም በያኔው ሰላሌ አውራጃ ደገም ወረዳ ውስጥ ነው። የ1ኛ ደረጃ ትምህርቱን ፍቼ ከተማ ተምሯል፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ደግሞ በወሊሶ ነው።
ከኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በመምህርነት ተመርቆ ወደ ጎንደር በማቅናት በመምህርነት ካገለገለ በኋላ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመርቋል።
ሙያው መምህርነት እና ጋዜጠኝነት ሲሆን፣ በጋዜጠኝነቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ፕሬስ መምሪያዎች ሠርቷል። ከጦር ግንባር ጋዜጠኝነት እስከ ኪነጥበባት ዘርፎች ሐያሲነት የዘለቀ ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ አበርክቶውን ጀባ ብሎናል።
ሁለገብ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የሆነው አበራ ለማ የሙዚቃ ድርሰቶችንም ይጽፋል። ከጻፋቸው የዘፈን ግጥሞች መካከል "ሀገሬ አትንኳት" የሚለው እና ጌታቸው ካሳ የዘፈነው በብዙዎች ኢትዮጵያውያን ልብ ታትሞ የሚኖር ሙዚቃ ነው።
የጦር ሜዳ ዘጋቢነቱ "የጦር ሜዳው ቀሲስ" የሚል ቅጽል ያሰጠው ሲሆን፣ ምርጥ የጉዞ ማስታወሻዎች አጠናቃሪም ነው። ለህይወት የሚያሰጉ አደጋዎችን ተጋፍጦ በጦርነት መሀል ሆኖ ሁነቱን በቀጥታ መዘገቡ አድናቆትን አትርፎለታል።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሆኖ አገልግሏል። በአሁኑ ጊዜ የሚኖረው በኖርዌይ ሲሆን፣ በኖርዌይ ደራስያን ማኅበር ብቸኛው እና የመጀመሪያው ጥቁር እንዲሁም በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚጽፍ አባል ደራሲ ነው። በዚህ ማኅበር ውስጥ የዓለም አቀፍ ኮሚቴው የረዥም ዘመን አባል በመሆንም ይታወቃል። ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንን እና ትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ የአስመራውን እስረኛ ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅን ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ሽልማት በእጩነት አቅርቦ እንዲሸለሙ አድርጓቸዋል።
ጋዜጠኛ እና ደራሲ አበራ ለማ በርካታ የታተሙ ሥራዎችን አበርክቶልናል። የማኅበረሰቡን ወግ እና ልማድ በደንብ ከሚያስነብቡን ድርሰቶቹ መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡- "ኩል ወይስ ጥላሸት" የግጥም መድብል፣ "ሽበት" የግጥም መድብል፣ "ሕይወትና ሞት" የአጫጭር ልብወለዶች መድብል፣ "ሞገደኛው ነውጤ" ኖቭሌት፣ "አባደፋር" ከሌሎች ደራስያን ጋር፣ "ጽጌረዳ ብዕር" ከሌሎች ገጣሚያን ጋር፣ "የማለዳ ስንቅ" የአጫጭር ልብወለዶች እና ግጥሞች መድብል፣ "መቆያ" የአጫጭር ልብወለዶች እና ግጥሞች መድብል፣ "ትዝታን በጸጸት" የቻይና የአጫጭር ልቦለዶች ትርጉም በጋራ፣ "አውጫጭኝ" የግጥም መድብል፣ "ሙያዊ ሙዳዬ ቃላት" ኢ-ልብወለድ፣ "የእውቀት ማኀደር" ኢ-ልቦለድ፣ "እውነትም እኛ" የግጥም ስብስብ በዲቪዲ፣ "2ዐዐ3 ጥሎ ማለፍ" ታሪካዊ ልብወለድ፣ "ውስጠት" የግጥም እና አጫጭር ልብወለዶች፣ "ሽፈራው-ሞሪንጋ" ኢ-ልብወለድ፣ "ቅንጣት-የኔዎቹ ኖቭሌቶች" የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ፣ "ኩርፊያ እና ፈገግታ" የግጥም መድብል፣ "የኢትዮጵያውያን ገጣሚያን ሥራዎች ወደ ራሽያ ቋንቋ የተተረጎመ" በጋራ፣ "ULIKE HORISONTER (ኖርዌጂያንኛ ግጥሞች)" በጋራ፣ "ENKETRØSTREN (በኖርዌጂያን ኖቭሌቶች)"፣ "TIME TO SAY NO (የእንግሊዝኛ ግጥሞች)" በጋራ፣ "ትውስብ" የአጫጭር ልብወለዶች እና ኖቭሌቶች ስብስብ ይገኛሉ።
በቅርቡ ደግሞ ከልብወለድ እና ግጥም ሥራዎቹ ወጣ ያለ እና የዓለማችንን ሳይንሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች አስደናቂ ነገሮችን ያካተተ "የዓለማችን ምስጢራት" የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባቢዎቹ አበርክቷል። ይህ መጽሐፍ ለቀጣዩ ትውልድ የምርምር መነሻ፣ ለትላልቆቹ ደግሞ ያሳለፉትን ወደ ኋላ መለስ ብለው እንዲመለከቱበት የሚረዳ እንደሆነ ተናግሯል።
በአበራ ለማ ከተደረሱት አጭር ልበወለዶች መካከል ሞገደኛው ነውጤ በፍቃዱ ተ/ማርያም በሬዲዮ ተተርኮ ተወዳጅነት ያተረፈ እና እስካሁንም እንደ አዲስ የሚሰማ ሥራ ነው።
በሥራዎቹ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል። ከእነዚህ ሽልማቶች መካከልም፡- በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሕይወት ዘመን ምርጥ ጋዜጠኛ፣ በሥነ ጽሑፍ አስተዋጽኦ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የክብር ሜዳይ ተሸለሚ፣ በሰሜን ኮርያ የሥነ ግጥም ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ፣ በጣሊያን ዩዲንዜ የበጎ ሰውነት የዋንጫ ሽልማቶች ናቸው።
በለሚ ታደሰ