ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል የምታደርገው ጥረት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ዋና አካል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለፁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የአለም የንግድ ድርጅት የአዲስ አባል አገራት ድርድር የስራ ዘርፍ ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን የምትቀላቀልበትን ሂደት ማፋጠን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ በኩል የአለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እየተደረጉ ያሉ ቴክኒካል ድርድሮች በፍጥነት አልቀው ድርጅቱን ለመቀላቀል በመንግስት በኩል ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት እንዳለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንና በዚህ ረገድ አጋዥ የሆኑና ከንግድና ፋይናንስ ዘርፉ ጋር የተያያዙ አስፈላጊ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና ውሳኔዎችን ኢትዮጵያ ማሳለፏን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት አገር እንደመሆኗ የአለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ ለድርጅቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አክለው ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተር ማይካ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የጀመረችውን የድርድር ሂደት ለማፋጠን የድርጅታቸው ሴክሬታሪያት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል።
ሁለቱ ኃላፊዎች ይህንኑ ሂደት ለማገዝ በሚያስችሉ ዝርዝር የቴክኒክ ስራዎች ላይ መምከራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።