ሞታችንን ለምን ይዘን እንዞራለን? 12 ሚሊዮን ሰዎችንስ ለምን እናጣለን?

8 Mons Ago 806
ሞታችንን ለምን ይዘን እንዞራለን? 12 ሚሊዮን ሰዎችንስ ለምን እናጣለን?

ሰዎች በተፈጥሮ ሂደት ኖረው መሞታቸውን ላሰበ ሰው ሞቱን ይዞ የሚዞር ፍጡር ስለመሆኑ ሊገነዘብ ይችላል። ደግሞም ሰው እያወቀም ሆነ ሳያውቅ መጥፊያው የሆነን ነገር በተደጋጋሚ እየከወነ ሞቱን ሲያፋጥን መመልከት ምነው ሰው ሞቱን ይዞ ለመዞር ፈቀደ ሊያስብል ይችላል።

በሰዎች በተደጋጋሚ የሚከወኑ ድርጊቶች አንዳንዴ ጠቃሚ እንደሆኑ ሁሉ ጎጂም ሆነው እስከ ሞት ሲያደርሱ የተመለከትንባቸው ሂደቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ።

ለዚህም ነው አንድን ተደጋጋሚ ድርጊት በመመልከት ይሄ ነገር ማህበረሰባዊ ጥፋት ያመጣል እና ከወዲሁ መላ ይበጅለት የሚሉ ሀሳቦች በባለሙያዎች የሚቀርቡት።

ከእንደዚህ ዓይነት ማህበረሰባዊ ጉዳትን ያስከትላሉ ከሚባሉ ልማዳዊ ድርጊቶች ውስጥ አንዱ ታዲያ የአካባቢ ንፅህና ጉድለትን የሚያመጡ ድርጊቶች ስለመሆናቸው መጥቀስ ይቻላል።

እንዲህ ያለው ችግር በእኛም ሀገር እየተስተዋለ በተለይ በአዲስ አበባ ደግሞ የጉዳቱም መጠን እያደገ በአካባቢ ብክለት የሚመጡ የጤና  እክሎች በአየር፣ በውኃ እና በአፈር ላይ ለሰዎች ጠንቅ መሆናቸው ይነገራል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሪት ሀና  በላይ  የሕክምና እክል ገጥሟቸው ወደ ህክምና ቦታ ሲያቀኑ የሳይነስ ሕመም መሆኑ እና ይህም የሚመጣው  ከአካባቢ መበከል ጋር በተያያዘ  መሆኑን  እስኪነገራቸው ጉዳዩን በትኩረት አይተወት እንደማያውቁት ያስረዳሉ።

ህክምናቸውን ከወሰዱ በኋላ የአካባቢ ንጽህና ላይ እንደቀላል የሚወሰዱ ልምዶች አደገኛ መዘዝ እንደሚያመጡ ተረድቻለሁ የሚሉት ወ/ሪት ሀና፤ የአካባቢ ንፅህና ከግል የቆሻሻ አወጋገድ ጋር የተያያዘ ነውም ይላሉ።

ብዙዎች የአካባቢ መቆሸሽን እና ወደ ብክለት መሸጋገርን ቀለል አድርገው ቢወስዱትም፤ እንደ ስትሮክ እና ካንሰር ለመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎች ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ የሳንባ  እና  የጽኑ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አስቻለው ወርቁ  ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን ሃሳብ ነው የሚያጠናክሩት።

ዶ/ር አስቻለው እንደሚሉት፤ የአካባቢ ንጽህና ባለመጠበቁ ምክንያት ቀላል በሽታዎች ከሚባሉት የቆዳ አለርጂ፣ ጉንፋን፣ አስም ጀምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንደ ስትሮክ፣ የልብ እና የሳንባ ህመም ብሎም እስከ ካንሰር ለሚደርስ ችግር ያጋልጣል።

ለአካባቢ ንጽህና አለመጠበቅ ዋናው ምክንያት የነዋሪዎች የቆሻሻ አወጋገድ ልማዳዊነት ነው የሚሉት በአዲስ አበባ አከባቢን በማስዋብ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ መንግስቱ ዘመነ "የነዋሪዎች ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ችግር በመኖሩ  ስራችንን በአግባቡ እንዳናከናውን እንቅፋት እየገጠመን ነው" ብለዋል።

አካባቢ ቆሻሻም ሆነ ጽዱ ሰዎች ባገኙት ቦታ ሁሉ የመጻዳዳት ልምድን እንዳስተዋሉ የሚናገሩት አቶ መንግስቱ፤ የእርምት እርምጃ መውሰድ ተገቢ እንደሆነም ነው የሚያነሡት፡፡

በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ12 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተገናኘ በሚከሰቱ በሽታዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ጥበቃ ማህበር ያጠናው ጥናት ያሳያል፤ ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የህዝብ ብዛት መጨመር እና ከተሜነት እያደገ ሲመጣ የአካባቢ ብክለት እየጨመረ እንደሚሄድ የሚናገሩት ዶ/ር አስቻለው ወርቁ፣  በአካባቢ ብክለት ሳቢያ የሚመጡ አንዳንድ በሽታዎች ከሀገር ውጭ የሚታከሙ መሆናቸውንም አንስተዋል።

እንዲህ ያለው ሁኔታ ደግሞ ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ጫና የሚያሳድርም ጭምር መሆኑንም ነው ዶ/ር አስቻለው የገለጹት።

በሜሮን ንብረት 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top