በቻይና ብረታ ብረቶችንና የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን በማምረት የሚታወቀው ዘኒት ስቲል ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፤ የኩባንያውን ዋና ስራ አስኪያጅ ሊዎን ዶንጋ እና የስራ ኃላፊዎችን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ የውጭ ባለሃብቶች ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ቻይናውያን መሆናቸውን የገለጹት አቶ አክሊሉ፤ለዚህም ኮርፖሬሽኑ የቻይና ኢንቨስትመንት ዴስክን ከፍቶ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የኩባንያው ኃላፊዎችም፤ ስለ ኢንቨስትመንት ዕቅዱ እንዲሁም ኩባንያው ያለበትን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ እና በመጀመሪያ ምዕራፍ ሊያከናውኗቸው ስላሰቧቸው ስራዎች አብራርተዋል።
ኩባንያው ወደ ስራ ሲገባም፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ 30 ሄክታር የለማ መሬት በመረከብ ከ150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ እንዳላው ተጠቁሟል።
በቀጣይም ኩባንያው በሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ከ100 ሄክታር በላይ የለማ መሬት በመረከብ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን መግለጹን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።