የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡- ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ

8 Mons Ago 686
የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡- ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ
የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
 
"ብክለት ይብቃ-ሁሉም ይንቃ" በሚል መሪቃል የተጀመረው ሀገር አቀፍ የአካባቢ ብክለትን የማስወገድ ንቅናቄ በአማራ ክልል የማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
 
በንቅናቄው የክልሉ ርዕሠ መስተዳር አረጋ ከበደ፣ የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን አለምነህ፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት እና የኅብረተሠብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
 
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች እና በተፈጥሮ መካከል በተዛባ ግንኙነት የሚፈጠር ክስተት በመሆኑ፤ በተፈጥሮ ላይ የተመረኮዘውን የሰው ሕይወት የተሻለ ለማድረግ ይህን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
 
ባለፉት ሦስት ዓመታት በፖሊሲ በተደገፈ መልኩ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ የልማት መርሐ-ግብር ውጤት የተገኘበት ስለመሆኑ ያነሱት ርዕሠ መስተዳድሩ፤ የአካባቢ ደህንነት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ ለንቅናቄው ተግባራዊነት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።
 
የክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው፤ ንቅናቄው በክልሉ የሚታየውን የፕላስቲክ፣ የውኃ፣ የአፈር እና የድምፅ ብክለቶች ላይ ለውጥ ለማምጣት ማስቻልን ያለመ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።
 
ለ6 ወራት በሚቆየው የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውኃ፣ የአፈር፣ የድምፅ ብክለትን መከላከልን ጨምሮ የአካባቢ እና የተፈጥሮ ተፅዕኖ ግምገማ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
 
በራሔል ፍሬው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top