የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ተገለጸ

12 Days Ago
የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ተገለጸ

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመላክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በአካል በመገኘት የዩኒቨርሲቲውን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል፤ የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንን እና ሰራተኞችም አወያይቷል።

በውይይቱ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ችግሮቹን በትዕግስት በመቋቋም የመማር ማስተማር ስራው እንዲጀመር በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ መንግስት ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ነገሪ (ዶ/ር)፤ አሁንም በዩኒቨርሲቲው እና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በችግርነት የሚነሱ የበጀት፣ ውዝፍ የደመወዝ ክፍያዎችና ሌሎች መንግስት ደረጃ በደረጃ እየፈታቸው የሚሄዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የሰላም ግንባታ እና የመማር ማስተማር ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ተገቢው የስነ-ልቦና ድጋፍ እና የማካከሻ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ለፈተና ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የተፈጠረው ችግር ሁሉ የሚያልፍ እና ነገ የተሻለ እንደሚሆን ሁሉም አካል በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲውን ወደነበረበት መመለስ ብቻ ሳይሆን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚገባም ነው ዶ/ር ነገሪ ያሳሰቡት።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋና ሀጎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ከሚገኙ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ እንደነበር ጠቁመው፤ በግጭት ውስጥም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን እንዳላቆመ እና ያለምንም ደመወዝ የህክምና፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ጆርናሎችን የማሳተም ስራዎችን ሲስራ እንደነበር ገልፀዋል።

አክለውም አሁን ላይ ከመንግስት ለዩኒቨርሲቲው በጀት ቢለቀቅም በጀቱ ዩኒቨርሲቲው ለሚያደርገው የጥናትና ምርምር ስራ፣ ለሚሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት በቂ አለመሆኑንም ነው የጠቆሙት።

አያይዘውም በበጀት እጥረት ሳቢያም ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል አደጋ ላይ መውደቁንና ለመምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች የ16 ወራት ውዝፍ ደመወዝ አለመከፈሉን በችግርነት አንስተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የበጀት እጥረት እንዲፈታ ለሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱን ዶ/ር ፋና ጠቁመው፤ ጥያቄው ፖለቲካዊ ውሳኔን የሚጠይቅ ጭምር በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top