በጋምቤላ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በጋራ የተጀመሩ የሰላምና የልማት ስራዎች እንደሚጠናከሩ ተገለጸ

19 Days Ago
በጋምቤላ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በጋራ የተጀመሩ የሰላምና የልማት ስራዎች እንደሚጠናከሩ ተገለጸ
በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የተጀመሩ የጋራ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ።
 
የጋምቤላ እና የኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፍረንስና የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ነው።
 
የኦሮሚያ፣ የጋምቤላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሮምሳ ሰለሞን በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው የአብሮነት ትስስር ይጠናከራል።
 
በሁለቱ ክልሎች ተጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች የተጀመሩ የጋራ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማጠናከር የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
 
የዛሬው የሰላም ኮንፍረንስና የምክክር መድረክ ዋና ዓላማም በሁለቱ ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች የተጀመሩ የጋራ የሰላምና የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በመሆኑም ከሁለቱ ክልሎች ተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የተገኙ ተሳታፊዎች ለአካባቢው የጋራ ሰላምና ልማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 
የጋምቤላ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አኩዋይ ኡጁሉ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በሰላም፣ በልማትና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
 
በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ በሚገኙት የሰላምና የልማት ስራዎችም አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
 
በተለይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጋምቤላ ከተማ የትምህርት ልማት፣ ተደራሽነት እና ጥራት እንዲጠናከር ያስገነባውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዓብይ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
 
ኮንፍረንሱ በጋራ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ምክትል ከንቲባው መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
 
በጋራ የሰላም ኮንፍረንስና የምክክር መድረኩ ላይ ከተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሐይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች እየተሳተፉ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top