ለመኸር ግብርና የሚውል 348ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ተገለፀ

1 Mon Ago 242
ለመኸር ግብርና የሚውል 348ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ተገለፀ

በትግራይ ክልል ዘንድሮ ለሚከናወነው የመኸር እርሻ 348 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መግባቱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

የፌዴራል መንግስት የአፈር ማዳበሪያው ቀድሞ ወደ ክልሉ እንዲገባ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም ቢሮው ገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ከደነው እንደገለፁት፣ ለዘንድሮ የምርት ዘመን አገልግሎት የሚውል 348ሺህ ኩንታሉ ወደ ክልሉ ገብቷል።

የማዳበሪያው ቀድሞ መግባት የእርሻ ስራውን ለማሳለጥ ጠቀሜታው የጎላ ነውም ብለዋል።

ለዘንድሮው የምርት ዘመን አገልግሎት የሚውል 700 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት ማቀዱንም ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል።

ዘንድሮ ወደ ክልሉ የገባውን የአፈር ማዳበሪያ አምና ከተረፈው አንድ መቶ ሺህ ኩንታል ጋር በማካተት ወደ ተለያዩ ወረዳዎች የማሰራጨት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ግብርና ሚኒስቴር የአፈር ማዳበሪያው ወደ ክልሉ ቀድሞ እንዲገባ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን አቶ አበራ ገልጸዋል።

አሁን ወደ ክልሉ ከገባው በተጨማሪ የዕቅዱን ቀሪ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በመጪው የመኸር ግብርና ከክልሉ 22 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የፌዴራል መንግስት፣ ባለሃብቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አርሶ አደሮችም ዘርን በመሰብሰብ ሂደት በትኩረት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top