የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅትን አስመልክቶ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅ የቀድሞ የባለሙያዎች ቡድን አባል ማርሸት ታደሰ (ዶ/ር) እና የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅ የቀድሞ የባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑ ሲሳይ አስፋው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዝዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሀገራት ከግጭት እና ከተለያዩ ጨቋኝ ስርዓቶች ለመውጣት መፍትሄ የሚሰጥ፣ ነገን ለማበጀት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲሁም እርቅን ለማበረታታት ከመደበኛው የፍትሕ ስርዓት ወጣ ያለ የመሸጋገሪያ መንገድ ስለመሆኑ (ዶ/ር) ማርሸት ታደሰ ይገልጻሉ።
በዓይነታቸው እና በመጠናቸው ሰፋ ያሉ ችግሮች እና ጥያቄዎች ሲኖሩ፤ በመደበኛው የፍትህ ስርዓት ብቻ መልስ መስጠት አይቻልም ያሉት ማርሸት፤ ለዚህም ከመደበኛው ስርዓት ውጭ የሆነ መሸጋገርያ መንገድ እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በሽግግር ውስጥ ማለፏን አስታውሰው፤ እነዚህም ሽሽግሮች በተወሰነ መጠን መፍትሔ ቢያስገኙም ዘላቂ ሰላም እና እርቅ ፍትሕ ማስገኘት አለመቻላቸውን ነው የገለጹት፡፡
ለዛሬ ግጭቶች እና አለመግባባት እንደ ምክንያት ሆነው የሚያገለግሉ ትናንቶቻችንን በተገቢው መንገድ አዋህደን በሽግግር ፍትሕ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው አላማው ይሄው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ ስርዓቶች ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ደግሞ ሲሳይ አስፋው ናቸው። ፖሊሲው ለተጎዱ ወገኖች ማካካሻን የሚፈጥር ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሲሳይ፤ የወንጀል ተጠያቂነት እውነትን ማፈላለግ እና የእርቅ ተግባር እንደሚጠቀስ አንስተዋል። ሀገሮች እነዚህን ስልቶች በመከተል የሽግግር ፍትሕን ማሳካት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ህዝብን ያሳተፈ መሆኑን በማንሳት፤ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ለማስቻል የተለያዩ መድረኮች መከናወናቸውን ነው የጠቆሙት፡፡