የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰባዊ ንቃት ማደግ አለበት - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

9 Mons Ago 735
የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰባዊ ንቃት ማደግ አለበት - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

የሴቶች እና የልጃገረዶችን ጥቃት ለመከላከል ማህበረሰባዊ ንቃት ማደግ እና ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ  መላኩ ባዩ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሴቶችና ታዳጊ ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ መደበኛ ክስተት የሚሰሙ ሆነዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ጥቃት ሰብዓዊ ክብር የሚያጎድፍ፣ የጤና፣ የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳቶችን የሚያደርስ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም ድርጊቱ አልቆመም ያሉት ኃላፊው፤ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ወንጀሎች እየተበራከቱ መጥተዋል ብለዋል።

ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆም እና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሴቶች ላይ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት ዝም ባለማለት እና ወንጀለኛን አጋልጦ በመስጠት ረገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የፍትህ አካላትም እንደዚህ አይነት ወንጀል በሚፈፅሙ አካላት ላይ ተመጣጣኝ እና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ህጉን ተከትለው ቢሰሩ ለችግሩ አንድ መፍትሄም እንደሚሆን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ተጎጂዎች ፍትህ እንዲያገኙ ማስቻል፣ ከፍትህ ባሻገርም የስነ₋ልቦና፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ ድጋፎችን እንዲያገኙና ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ዘላቂ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ጥቃት ከመድረሱ በፊትም ሆነ እየደረሰ ባለበት ሰዓት ጥቆማ ለመስጠት የሚያስችል የመረጃ አገልግሎት በየክልሉ መጀመሩን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ አስተዳደር፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካለት ጋር በመቀናጀት የቅጣት አድራሾች መረጃ ምዝገባ  ሶፍትዌር መዘርጋቱን አንስተው፤ ይህም እንደዚህ አይነት ጥቃት አድራሾች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ያግዛል ብለዋል፡፡

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top