የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 932 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡንም ጽህፈት ቤቱ ጠቅሷል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም እንደገለፁት በተያዘው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት 931 ሚሊዮን 984 ሺህ 102 ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
ከዚህም ውስጥ ከ767 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከቦንድ ሽያጭና ስጦታ እንዲሁም ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ከዳያስፖራው ድጋፍ መገኘቱን አመልክተዋል።
8100 አጭር የጽሁፍ መልዕክት እና የኢትዮጵያ ነጻ አካውንት በሚል ስያሜ ባለው የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጭም ለሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ነው የጠቆሙት።
የሕዳሴ ግድቡ በኢትዮጵያውያን አቅም ብቻ እየተገነባ ያለ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የግድቡ ግንባታ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት ”በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሀ ግብሮች በመከበር ላይ እንደሆነም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መጣሉ ይታወቃል።