በሶማሌ ክልል ሩዝ በመስኖ የማልማት ንቅናቄ ተጀመረ

1 Mon Ago
በሶማሌ ክልል ሩዝ በመስኖ የማልማት ንቅናቄ ተጀመረ
በሶማሌ ክልል ከ2ሺ እስከ 3ሺ ሄክታር ማሣ ላይ ሩዝ በመስኖ የማልማት ንቅናቄን የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ እና የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ በሸበሌ ዞን አስጀመሩ።
 
በአንድ ሄክታር 45 ኩንታል በማምረት በመስኖ ከሚለማው ከ2ሺ ሄክታሩ 90 ሺህ ኩንታል የሩዝ ምርት ለመሠብሰብ ታቅዷል።
 
በቀጣይም በሄክታር የሚለማውን ምርት መጠን ከ45 ኩንታል ምርት፤ ወደ በአንድ ሄክታር 50ኩንታል እና ከዛ በላይ በማምረት በ3 ዓመት ውስጥ 10 ሺህ ሄክታር ሩዝ በመስኖ በማልማት 5መቶ ሺ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን አስታዉቀዋል።
 
የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ የሩዝ መስኖ ልማቱ በሸበሌ ዞን ፣ አፍዴር ዞን ፣ ሊበን ዞን እና ሲቲ ዞን ይከናወናል ብለዋል።
 
የሩዝ ፍጆታ በኢትዮጵያ ፍላጐት እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ባለፉት አመታት በተሰራው ስራ 50 በመቶ ከውጭ የሚገባ ሩዝ ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ተችሏል ብለዋል የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ።
 
የሶማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ የሩዝ መስኖልማቱ የዉጭ ምንዛሪ ወጭን መቀነስ፣ገቢ ምርትን የመተካት እና በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ ነው ብለዋል።
 
ሶማሌ ክልል አሁንም በስፋት የመልማት ዕምቅ አቅም ያለው በመሆኑ፤ አሁንም ይህን መሰል ሰፋፊ የመስኖ ልማት ስራዎች መከናወናቸዉ ለክልሉ የግብርና ዕዉቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ርዕሰ መስተዳድር ተናግረዋል።
 
ለስኬቱም ክልሉ ቁርጠኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
 
በብሩክ ተስፋዬ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top