የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ባጋጠመው የመለዋወጫ እጦት ምክንያት መስጠት የሚገባውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የከተማዋ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ገለፀ፡፡
የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሮቤ መንገሻ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎቱን ሲጀመር የመለዋወጫ ጉዳይ ሳይታሰብበት በመቅረቱ አሁን ላይ ችግር እንዲገጥም ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ የመለዋወጫ አቅራቢ ድርጅቶች እየተጠበቁ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በርከት ያሉ ባቡሮች ከስራ ውጪ እንዲሆኑ ምክንያት የሆነው የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የከተማዋን ትራንስፖርት የሚያቃልል እንዳይሆን ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የትራንስፖርት እጥረቱን ይቀንሳል ተብሎ ቢታሰብም እንደታሰበው መሆን አለመቻሉን ነው የገለፁት፡፡
ከዚህ በፊት ባቡሮቹ ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ ችግሮች ሲገጥማቸው እንደነበረ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ይህ ችግር ሲፈታ ደግሞ የመለዋወጫ እጦት ሌላኛው ችግር ሆኖ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ማግኘት አለመቻሉ ችግሩ በአጭር ጊዜ እንዳይፈታ ማድረጉን ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር አገልግሎት ላይ የገጠመው ዋናው የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር ከተፈታ በወራቶች ውስጥ ሙሉ ባቡሮቹ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻልም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሲመሰረት በ41 ባቡሮች አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 15 የሚሆኑ ባቡሮች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።
በየስድስት ደቂቃው በየመሳፈሪያ ጣቢያው በመድረስ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣል በሚል እቅድ ስራውን የጀመረው የቀላል ባቡሩ አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጥበት ሰዓት በእጅጉ ውስን ሆኗል።
በሜሮን ንብረት