ሀገር እንድትቀጥል በተለያዩ ዘመናት ደም ፈሷል አጥንት ተከስክሷል ሕይወትም ተገብሯል። ሀገር በአንድ ጀንበር አትገነባምና በየዘመኑ ሁሉም የየራሱ የሽንፈት እና የድል ታሪክ አለው።
ኢትዮጵያም በታሪኳ ብዙ ፈተናዎችን እየተሻገረች ድል እያደረገች በልጆቿ መስዋዕትነት የቆመች ሀገር ነች። የታሪክ ቀደምት ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ስትነሳ በዓለም ህዝብ ዘንድ በጉልህ ከሚታወሱ ታሪኮቿ ውስጥ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል መሆኗ ተጠቃሽ ነው።
የምናወራው ስለመውደቅ ወድቆ ሰለመነሳትም አይደለም፤ ይልቁንስ አንገትን ቀና አድርጎ ደረትን ነፍቶ እኛ ማንም ያልደፈረን ነፃ ህዝቦች ነን ብሎ ስለመቆም እንጂ።
ይህ ታሪክ እንዲህ ነው የሚጀምረው የአውሮፓ ኃያላን መንግስታት በዓለም ላይ ከኛ ውጭ ፈላጭ ቆራጭ፣ ገዢም አዛዥም የለም በሚሉበት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ ትልቅ ስብሰባ የጀርመኗ በርሊን ከተማ አስተናገደች።
እ.ኤ.አ 1884 የተከናወነው የበርሊን ስብሰባ ትልቁ አጀንዳና ምክንያት ደግሞ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደምን እንደሚቀራመቷት ለመቀየስ ነበር። ንግግሩና ውይይቱ ያተኮረው እንደምን በሚለው ላይ ብቻ ነበር፤ ለምን? እንዴት? የሰውን ሀገር መውረር ይቻላል የሚለው ጥያቄ ጉዳያቸው አልነበረም ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካውያን የቆዳቸው ቀለም ጥቁር በመሆኑ።
አስገራሚው ነገር እነዚህ አውሮፓውያን አህጉሪቷን በሙሉ በቅኝ ግዛት መያዝ መፈፀም ያለበት እንጂ የሚያከራክር ጉዳይ አልነበረምና ውሳኔውን ለመወሰን ምንም አልያዛቸውም፤ በዚህም መሰረት አውሮፓውያኑ አፍሪካን ተቀራመቷት።
ፈረንሳይ 34 በመቶ፣ እንግሊዝ 32 በመቶ፣ ጀርመን 7 በመቶ፣ ቤልጄም 7 በመቶ፣ ስፔን 7 በመቶ፣ ፖርቹጋል 6 በመቶ፣ ጣሊያን 5 በመቶ እና ነፃ ሀገራት 2 በመቶ ድርሻን ያዙ ሲሉ ተድላ ዘዮሃንስ የኢትዮጵያ ታሪክና ጣሊያን በኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል።
ይህ ሚዛን ነው እንግዲህ የጣሊያንን መንግስት ክብር የሚቀንስ ሆኖ በጣሊያን ባለስልጣናት ዘንድ የታየው። በዛን ጊዜ ጣልያን የያዘቻቸው የሊቢያ የሶማሊያና የኤርትራ ምድር አብዛኛው በርሃማ ሆነባት ስለዚህ ዓይኗን በኢትዮጵያ ላይ ጣለች።
ነገር ግን ጣልያን ጥሩ ገድ አልገጠማትም፤ ምክንያቱም የመጣችው አንነካም ከነኩንም አንለቅም፤ በሀገራችን አስተዳደር ብንከፋም እንኳን "ሀገራችን ሌላ አስተዳደር ሌላ" ብለው ክንዳቸውን ከፍ በሚያደርጉበት ኢትዮጵያውያን ቀዬ ነበር።
በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምኑትና ፈጣሪ ፈቅዶ በሰጠን ሀገራችን ላይ ማንም ከውጭ መጥቶ ሊያዘን፣ ሊገፋን ጉልበታችንን ሊበዘብዝ፣ በቆዳችን ቀለም ሊያጣጥለን አይችልም፤ ያሉት የኢትዮጵያ አርበኞች የሚሳሱለትን ቤታቸውንና ቀያቸውን ወደ ኋላ ትተው ጋሻ እና ጦራቸውን ታጥቀው የንጉሳቸውን ጥሪ ተቀብለው ፋሽስትን ወደ መጣበት ለመመለስ በፈረስ በበቅሎ አለፍ ሲልም በእግራቸው ወደ ዓድዋ ተራሮች ገሰገሱ።
ወረዱ ዓድዋ ላይ ጀግኖች ከየቤቱ
የልባቸው እሳት ተመዞ ካፎቱ
በዛ እንደብልጭታ መድፍና ጥይቱ
ዳናው በረከተ ፎከረ ካንጀቱ
የሰው የፈረሱ ጠፋው ምልክቱ
ታጥቆ ሰው ሊገዛ እጣው ቢደርስበት
ባመጣው መሳርያ ገናን ክንድ አርፎበት
የወደቀው ወድቆ ታሪክ ተፃፈበት
እንዳለው ዜመኛው ከእምዬ ኢትዮጵያ በፊት እኔን ያስቀድመኝ የሀገሬን ክፉ ከማይ ብሞት ይሻላል ባሉ ኢትዮጵያዊ ጀግና አርበኞች መስዋዕትነት እና በአፄ ሚኒሊክ፣ በእቴጌ ጣይቱ እንዲሁም በጦር መሪዎችና ራሶች አጋፋሪነት ጣሊያን በጥቁር ጀግኖች ድል ተመታች።
ይህ የሆነው እንግዲህ ከዛሬ 128 ዓመታት በፊት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር። ይህ ድል ለድል አድራጊዎች ኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካውያን እና ለመላው የጥቁር ህዝብ የአሸናፊነት መንፈስ ሲያጎናፅፍ፤ በአንፃሩ የጣሊያን ሽንፈት ነጮችን በጦርነት መርታት እንደሚቻል ለመላው የዓለም ህዝብ ያሳየ ክስተት ሆነ።
ድሉን ተከትሎም የኢትዮጵያን በነፃነት መኖር የወቅቱ ኃያላን ሀገራት እንግሊዝና ፈረንሳይ ግልፅ እውቅና እንዲሰጡ አደረጋቸው።
ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ጣሊያንን ጨምሮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሀገርነት ተራ በተራ ተቀበሉ ። የጣሊያን ተሰሚነት በጊዜው በዓለም ሀገራት ዘንድ ሲቀንስ የኢትዮጵያ ድልና ዝና በመላው ዓለም ናኘ።
ዛሬ አንገታችንን ቀና አድረገን እኛኮ የእነዛ ጀግና ልጆች ነን ብለን እንድንኮራ የሆነው ያኔ አባቶቻችን ከሰሜን ከደቡብ ከምዕራብና ከምስራቅ ተጠራርተው የቤታቸውን ችግር እና የአስተዳደርን ኩርፍያ ወደጎን ትተው በዓድዋ ተራሮች ግርጌ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው።
ዛሬም ሀገር እንድትቀጥል የዘመናችን ፋሽስት ሆኖ ፊታችን ላይ የቆመውን ድህነትና ፅንፈኛ ብሔርተኝነት እንቢ ብለን በማስወገድ በአንድነት ሀገራችንን እንድንገነባና ዳግማዊ ዓድዋን በዚህ ዘመን እንድንፅፍ ይጠበቃል።
ምስጋና ትላንት በደማቸው ሀገርን አፅንተው ዛሬን ቀና ብለን እንድንሄድ ላደረጉን አባቶቻችን።
እንኳን ለ128ተኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!